Page 118 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 118

ደስታ መብራቱ


                  የፖለቲካችንን  ህመሞች  ለማከም  የምናደርገው  ጥረት  በኢኮኖሚው  መስክ
           ሊመጣ  በሚገባው  ለውጥ  ካልታገዘ  ውጤታማነቱ  አጠራጣሪ  በመሆኑ፣  የመጽሃፉ
           የመጨረሻ  ክፍል  በሃገራችን  ውስጥ  አካታች  እና  ዘላቂ  ልማት  ለማረጋገጥ  መታየት
           የሚገባቸውን  አበይት  ነጥቦች  ተመልክቷል።  ይህም፣  ፖለቲካችንን  ጤናማ  ከማድረግ
           ባሻገር በከፍተኛ መጠን እያደገ ላለው ወጣት የሥራ እድል ለመፍጠር እና የአጠቃላዩን
           ህዝብ ማህበራዊ ሁለንተናዊ ደህንነት ለማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝባል።
           ይህንንም  ለማሳካት፣  የአጠቃላይ  ህልውናችን  ዋነኛው  መሰረት  የሆነውን  የተፈጥሮ
           አካባቢያችንን  መንከባከብ  እና  የዚህ  ምዕተ  ዓመት  ወሳኝ  ገጽታ  ከሆነው  ከአራተኛው
           የኢንዱስትሪ አብዮት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ፈተናዎችን ለመቋቋም እና እድሎቹንም
           ለመጠቀም ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል። በዚህ ረገድ፣ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ጊዜው
           በሚጠይቀው እውቀት እና ክህሎት ራሱን በማስታጠቅ የራሱንም ሆነ የሀገሪቱን የወደፊት
           እጣ ፈንታ የመወሰን ታላቅ ድርሻ እና ሃላፊነት እንዳለበት መገንዘብ ይኖርበታል። ለዚህም፣
           ከምህዳራዊ  አስተሳሰብ  ጋር  ተያያዥነት  ያላቸውን  እና  ፈጣን  በሆነ  ሁኔታ  እየበለጸጉ
           በመሄድ ላይ ያሉ አስተሳሰቦችን ከሃገራዊው ፍላጎት እና ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለመተግበር
           መጣር ይኖርበታል።
                  በመጨረሻም፣ መጪው ሃገራዊ ምርጫ በሃገራችን ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ
           ጊዜ በህዝብ ዘንድ የተሻለ ይሁንታ ያገኘ ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ሥርዓት ለመመስረት
           የሚያስችል  መልካም  አጋጣሚ  እንደሆነ  ይነገራል።  ይህ  እንዲሆን፣  ሁሉም  የሃገራችን
           የፖለቲካ መሪዎች፣ ልሂቃን፣ ቀስቃሾች እና የሚዲያ ባለሙያዎች ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ
           እንዲሆን ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን
           ምን፣ የዴሞክራሲያዊው ሥርዓት ምስረታ ጅማሮ በመሆኑ በተከታዮቹ ዓመታት በርካታ
           ቀሪ  ስራዎች  እንደሚኖሩ  መታወቅ  ይኖርበታል።  በዚህ  መጽሃፍ  የተነሱት  ሃሳቦች
           በመጪው ዓስርተ አመታቶች የሚጠብቁንን በርካታ የፖለቲካ እና የዘላቂ ልማት ስራዎች
           ከስሜታዊነት  ይልቅ  በፋና-ወጊ  እና  ሩቅ  አሳቢ  አመለካከት  እንድንወጣ  የበኩሉን
           አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ።
   113   114   115   116   117   118   119   120   121   122