Page 4 - Ethiopia in the Bible by Abune Petros 2
P. 4
መጽሐፍ ቅዱስ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም የተጠቀመበት ምክንያቱ ምንድን ነው ? የሚለውን ጥያቄ በቦታው
እንመለከተዋለን ።
በዚህ ቦታ ላይ ግን ለዚህ ጽሑፍ አነሣሽ ምክንያት የሆነው ዐቢይ ጉዳይ በጀርመን ሀገር በተካሄደ የመጽሐፍ ቅዱስ
የትርጉም ሥራ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል እንዳይኖር የመደረጉን አግባብነት ከክርስትና ሥነ መለኮት ፣ ከሥነ ልሳንና
ከታሪክ አኳያ መዝኖ ማየት ነው ።
በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ በጀርመን የሥነ መለኮት ትምህርታቸውን ተምረው የዶክትሬት ድግሪ መመረቂያ ሥራቸውን
የሠሩ ዶክተር በንቲ ኡጁሉ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ፥ የጀርመን ወንጌላዊት ሉተራን ቤተ ክርስቲያን ባሳተመችው አዲስ
የጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚለው ስም እንዳይኖር የተደረገው ኢትዮጵያ የሚለው ስም ስድብ ስለ ሆነ
ነው ብለው ተናግረዋል ።
እንደ እርሳቸው አባባል ከአርባ አምስት ጊዜ በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰው “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል በሙሉ
ትርጉሙ ኩሽ መባል አለበት ፤ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም የትርጉም ሥራቸውን በሚያሻሽሉበት ጊዜ ይህንኑ
ፈለግ መከተል አለባቸው ይላል ። ይህን ሐሳባቸውንም እንዲህ ይገልጡታል ። “የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከመካከለኛው
ዘመን ጀምሮ እየተካሄደ ያለ ነገር ነው ። ከየትርጉም ሥራው ጀርባ ያለው ሐሳብ በቀድሞዎቹ ኅትመቶች ውስጥ የተወሰኑ
ጉድለቶችና ግድፈቶች ይኖራሉ” ከእነዚህ ስሕተቶች አንዱ ደግሞ በዕብራይስጡ ኩሽ ተብሎ የቀረበው ወደ ግሪክ ሲተረጎም
ኢትዮጵያ ተብሎ መተርጎሙ ነው ።
የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት መጽሐፍ ቅዱስን ሲተረጉሙ ኑረዋል ። ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም ።
በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ማርቲን ሉተር መጽሐፍ ቅዱስን ከላቲን ወደ ጀርመንኛ ከተረጎመበት ጊዜ ጀምሮ የቋንቋና
የሐሳብ ትርጉም እየተካሄደ እንዳለ ነው ። በነዚያ ትርጉሞች ውስጥ ስህተቶች ነበሩ ። አንዳንዶቹ የቋንቋ ሌሎቹም
ግንዛቤያዊ ነበሩ ። አሁን እየተካሄደ ላለው ትርጉም ምክንያቱ እነዚያ ያለፉ ስህተቶች ናቸው” ይላሉ እኔሁ ሊቅ ።
ይህ ሲገባን ነው የዶክተር በንቲ ኢትዮጵያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ማውጣት እንዴት ትክክል ነው እንደሚሉ መረዳት
የምንችለው ። ክፍሉን እንደምንመለከተው ከሉተር የፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ ጀምሮ የመጽሕፍ ቅዱስ ትርጉሞች
እየተካሄዱ ነው ። የዚህ ሥራ ምክንያትም በቀድሞው የጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን “የቋንቋ ስሕተቶች”
ለማረም ሲሆን ፤ ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አግላይ ቃላት መኖር የለባቸውም የሚል ነው ።
ይህ አባባላቸው የዶክተር በንቲ የሥነ መለኮት ቅኝት ለዘብተኛ ሥነ መለኮት (Liberal Theology) የሚባለው
መሆኑን በሚገባ ያመለክታል ። ለዘብተኛ ሥነ መለኮት መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከተው እንደ አንድ ከፍተኛ ስፍራ
የሚሰጠው ባህል ወለድ ሥነ ጽሑፍ (Literary Cultural production) አድርጎ ነው ። ክርስትናንም የባህል
አንጻራዊነትን (Cultural relativism) በተተገነ መንገድ ብቻ ለማብራራት ይሞክራል ። ግብረ ገባዊ ዕሤቶችንም
ከሃይማኖት ገንጥሎ በራሳቸው ለማቆም ይሞክራል ። ለዘብተኛ ነገረ መለኮት ዘመናዊውን ዓለም ክርስቲያን ከማድረግ
ይልቅ ክርስትናን ከዘመኑ መንፈስ ጋር ለማስማማትና በዘመናዊ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ይጣጣራል
። ለዚህ ሲል ከሐዋርያዊ የክርስትና ትምህርት በእጅጉ የራቀ ፣ ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት የተፋታ የግብረ ገብ አስተምህሮ
ያስተምራል ።
ለምሳሌ ፦ በዘመናችን ያለውን የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ፖለቲካዊ ዕውቅና እንዲያገኝ የማድረግ ዘመቻ ክርስቲያናዊ
ጭምብል ለማልበስ ይሞክራል ። ለዘብተኛ ሥነ መለኮት ፣ ሲያሻው መጽሐፍ ቅዱስ ተመሳሳይ ጾታ አያወግዝም ብሎ
የዐይነ ደረቅ ክርክር ያቀርባል ። ክርክሩ አላዋጣ ሲል ደግሞ ጭራሽ “የተመሳሳይ ጾታ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የሚስማማ
መጽሐፍ ቅዱስ” እስከ ማዘጋጀት ይደርሳል ። ለዚህ ሁሉ ክሕደት የሚቀርበው ምክንያትም እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ
ስለሚወድድ ማንንም የሚያገልል ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖር የለበትም የሚል ነው። የዘመኑን ሰዎች ለማስደሰት
ሲል የእግዚአብሔርን እውነት ፣ የሐዋርያትን ትምህርት ፣ የአበውን ምስክር ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት በሙሉ
አሽቀንጥሮ ይጥላል ።
“.ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።” መዝሙረ ዳዊት - ም. 68 ቁ. 31 4