Page 9 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 9
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
ወፍ-በረር ምልከታ
በደራሲው የተሟላ ህይወት (fulfilling life) እሳቤ መደነቅ የጀመርኩት ከጥቂት
ዓመታት በፊት በርካታ ጥቅማጥቅሞች የታጨቁበትን፣ በተባበሩት መንግስታት የአካባቢ
ፕሮግራም የያዘዉንና ሊያገኝ ይችል የነበረዉን ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ በቃኝ ብሎ
ለመሰናበት የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባቱን ሲነግረኝ ነበር። ጤናውን የተጠራጠርን ያኔ
በናይሮቢ በተለያዩ የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት ዉስጥ የምንሰራ ኢትዮጵያዊያንና ሌሎች
ጓደኞቹ ጥቂት አልነበርንም። ከቁሳዊ ስኬት ባሻገር ብዙ ዋጋ ያላቸዉ፣ ለወጣበት ህብረተሰብ
ወረታ መመለስን ታሳቢ ያደረጉና ቀጣይ በሆነ አኳኋን ለመጭዉ ትዉልድ የረዥም ጉዞ
ስንቅ የሚሆኑ የብዙ ህልሞች ባለቤት እንደሆነ ያስተዋልነው ናይሮቢን ከለቀቀ በኋላ
የሚሰራቸዉን ስራዎች ስናይ ነው ። ይህ መፅሀፍ ከነዚህ ህልሞች አንዱ መሰለኝ። ከህልሞቹ
አንዱን በማሳካቱም ዉጭ ሃገር የተወለደችዉና ያደገቺው ልጄ ዲቦራ ነፍሷን ሐሴት
ሲሞላት እንደምትለው ደራሲዉን “እሰይ የኛ ጎበዝ” ልለው ወደድሁ።
ከተለመደው ወጣ ያለ ጭብጥ ይዞ መነሳቱ የመፅሀፉ አንዱ ፋና ወጊ ገፅታው
ይመስለኛል። የተወሳሰቡና ሙያዊ የሆኑ የምህዳራዊ አስተሳሰብ አላባዊያንና ተግባራዊ
አንድምታቸዉን በሃገራዊ ሁነቶች መመንዘሩና ቀላልና ጣፋጭ በሆነ አቀራረብ መቀመሩ
ደራሲዉ ብዙ ትጋትን የጠየቁ ሰፊ ማብሰልሰልንና መብሰልሰልን ያካተቱ ረዣዥም የሃሳብና
የምጥ ሌሊቶች እንደነበሩት ይጠቁማል። ከሁሉ በላይ የምህዳራዊ አስተሳሰብ የተጠየቅ
ስልትን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር አሰናስሎ ዛሬም ላልተገታው ማህበረሰባዊ ዉድቀታችን
መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸዉን ሃሳቦች ስፋት ላለው የሃገራችን ህዝብ ተደራሽ አድርጎ ማቅረቡ
ደራሲዉን ከበርካታዎቹ ዓይናአፋር ልሂቆቻችን ለየት አድርጎ ያቆመዋል። ይህ ምህዳራዊ
አስተሳሰብን ከሃገራዊ ማዕቀፍና ጭብጥ ጋር ያዋደደበት እና የልፋቱ ትሩፋት የሆነው
መፅሀፍ፣ ውይይቶችን የሚያጭር እና ለሃገራችን መቀጠል ሲባል ተረኮቻችንን እና
ዕሴቶቻችን የተዋቀሩባቸውን ጡቦች እንደገና እንድንጎበኛቸው የሚያበረታታ፣ ለተግባቦትና
ለመግባባት ጥቂት የማዕዘን ድንጋዮችን የሚያቀብል ድርሳን ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ።
በእነዚህ ላይ የታነፁ የአመለካከት ሽግግሮች ዕዉን ቢሆኑ፣ ያለውን እንካችሁ በማለቱ
ከሚሆነው በላይ በአማርኛ የበኩር ልጄ ባለውና በእኔ ዕይታ እጅግ ተነባቢና ጠቃሚ
በሆነው መፅሀፉ ጥልቅ እፎይታ የሚሰማዉ ይመስለኛል።
ደራሲው በቅንፍ ዉስጥ በእንግሊዝ አፍ ያመላከታቸው አንዳንድ ጉዳዮች
ለተጨማሪ ንባብ መንደርደሪያ የሚሆኑ ቁልፎች (key words) ማስቀመጥን መነሻ ያደረጉ
ሳይሆኑ አይቀርም ። እነዚህን በመጠቀም፣ ደራሲዉ በተለይ ሊደርስ የፈለገው አዲሱ
ትውልድ ያለማመንታት ተጨማሪ ንባብ በማድረግ፣ በምህዳራዊ አስተሳሰብ ለመራቀቅ፣
የሃገሩን ዉጣዉረዶች በአዲስ መነፅር ለማየትና ለመተንተን አዲስ የምናብ ፍኖት የቀደደ
ይመስለኛል - መፅሀፉ።
ዶ/ር ሰለሞን አበበ፣ የተባበሩት መንግስታት አቶሚክ ኢነርጂ ተቋም
1