Page 10 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 10

ደስታ መብራቱ


                  ሁሉም  አንዳቅሙ  የሃገሩ  ጉዳይ  ያሳስበዋል  ተብሎ  ቢገመት  ከዕውነተኛነት
           ብዙም አይራቅም። ሃገራዊ ችግርን ስናብሰለስል፣ ስሜትና ምኞታችን ትንታኔያችንን እና
           አቋማችንን  ይጫኑታል።  ከዚህ  ተነስተን  የምንደርስበት  ውሳኔም  ካለንበት  አዙሪት
           አላወጣንም። ፕሮፌሰር ደስታ መብራቱ ይህን በመገንዘብ ነው ከስሜታዊነት ወጥተን፣
           ምኞታችንንም ምክንያታዊ አድርገን እንድናስተውል የሚመክረን። በግሉ በሚያደርጋቸው
           ውይይቶችና በጽሁፍ በሚያቀርባቸው ሃሳቦች የሚጠቀምበትን ሳይንሳዊ ዘዴ ሊያካፍለን
           ይህችን ‘ምህዳራዊ አስተሳሰብ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ’ የምትል መጽሐፍ አቅርቦልናል።
                  በመጽሐፉ  ውስጥ  የምህዳራዊ  አስተሳሰብን  ታሪካዊ  አመጣጥና  ምንነት
           ለአብዛኛው  አንባቢ  ሊገባ  በሚችል  መልኩ  አቅርቦታል።      ይህ  ሳይንሳዊ  የውስብስብ
           ችግሮች መፍቻ ዘዴ ለተለያዩ የህይወት ዘርፎች የሚያገለግል በመሆኑ፣ ለህበረተሰብና
           ለሃገራዊ  ፖለቲካ  ችግሮቻችን  መፍቻም  ሊሆን  እንደሚችል  በምሳሌዎች  አስደግፎ
           ያሳየናል።  በሳይንሳዊ ሙያው ያካበተውን ዕውቀት፣ በማስተማር ሙያው የተጠቀመበትን
           ዘዴ፡  በግል  ህይወቱ  የሚተገብረውን  አስተዋይነት  በዚህ  መጽሃፍ  ውስጥ  በሚገባ
           አንጸባርቋል፡፡  የቃላት  አጠቃቀሙ  ግልጽነት  እንዲኖረው  አስፈላጊ  በሆነው  ቦታ  ሁሉ
           ለመግለጽ  የሚያስቸግሩ  የእንግሊዝኛ  ቃላትን  የአማርኛ  ትርጉም  እንዲያገኙ  አድርጓል፡፡
           በመሆኑም፣ ያልተለመዱ ሳይንሳዊ ቃላት ተብራርተው እናገኛለን፡፡ መጽሃፉ ለንባብ ብቻ
           ሳይሆን ለመማሪያም ሰለሆነ በያንዳንዱ ምዕራፍ ማጠቃለያ ላይ ዋና ዋና ነጥቦቹ ባጭሩ
           ቀርበዋል፡፡
                  በመሆኑም፣  በተለይም  ወጣቶች፣  ፖለቲከኞች፣  የፖለቲካ  ተንታኞች፣  እና
           በማንኛውም የስልጣንና የሃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ ግለሰቦች ከመጽሐፉ በርካታ ቁምነገሮችን
           እንደሚያገኙ  እገምታለሁ፡፡  በተለይ  ሃገራችን  ባሁኑ  ጊዜ  ያለችበትን  የተወሳሰበ  ሁኔታ
           አቅጣጫ ማስያዝ ሃላፊነቱ ለተጣለባቸው ወገኖች  ሁሌ ከስሜትና ከምኞት በመራቅ እና
           ምህዳራዊ  አስተሳሰብን  በመጠቀም  መፍትሄ  እንዲያገኙ  የፕሮፌሰር  ደስታ  መብራቱ
           መጽሐፍ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
                                              አቶ ብርሐነ መዋ፣ ሜሪላንድ፣ አሜሪካ

                  እውቁ  የኢኮኖሚክስ  ባለሙያ  ዶ/ር  እሸቱ  ጮሌ  በ1984  ባቀረበው  አንድ
           ጥናታዊ ጽሁፍ፣ ሃገሪቱ ሌላ መልካም የለውጥ አጋጣሚ ላይ እንደምትገኝ አውስቶ ይህንን
           የለውጥ ዕድል ማበላሸት በታሪክ ታላቅ ተወቃሽ እንደሚያደርገን አስጠንቅቆ ነበር። ከሰላሳ
           ዓመታት በኋላ በሌላ የለውጥ አጋጣሚ ላይ ከተመሳሳይ ሃገራዊ ጥያቄዎች ጋር ተፋጠን
           እንገኛለን። ፕሮፌሰር ደስታ፣ በምህዳራዊ አስተሳሰብ በመቃኘት ውስብስብ ችግሮቻችንን
           በአግባቡ መረዳት እና ወደ ዘላቂ መፍትሔ ማምራት እንደምንችል በዚህ መጽሐፍ አሳማኝ
           በሆነ መንገድ አቅርቦልናል። በዚህ ረገድ መጽሐፉ፣ ፊት ለፊታችን የተድቀኑብንን ፈተናዎች
           ለመሻገር ከሚኖረው አበርክቶት ባሻገር  ለመጪው ትውልድም ታላቅ ትምህርታዊ ፋይዳ
           ይኖረዋል።
                                            ዶ/ር  ጉልላት  ከበደ፣  ኒው  ስኩል፣  አሜሪካ
   5   6   7   8   9   10   11   12   13   14   15