Page 13 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 13

ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ


                     እንደመታደል  ሆኖ፣  የሙያ  ህይወቴም  በዘመናችን  ገኖ  ያለው  ዓለም  አቀፍ
             የኢኮኖሚ ሥርዓት (globalization) በምድራችን የተፈጥሮ ሚዛን ላይ የሚያስከትለውን
             መዛባት  ‘ለምን’  ብሎ  በመመርመር፣  ሁሉንም  አካታች  የሆነ  ዘላቂ  ልማት  ለማምጣት
             የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ማፈላለግ ላይ የሚያተኩር ሆኗል። በዚህ ሂደትም ውስጥ፣
             ውስብስብ  ችግሮችን  ባግባቡ  ለመረዳት  እና  መፍትሔ  ለመሻት  ምህዳራዊ  አስተሳሰብ
             (systems thinking) ያለውን አበይት አስተዋጽኦ ለመገንዘብ እና ለመረዳት ችያለሁ።
                     ዛሬ  በሃገራችን  ያለውን  የፖለቲካ  ምስቅልቅል  ስንመለከት፣በቀዳሚነት
             በማናቸውም ወገን ለሚወሰዱ የፖለቲካ አቋሞች  እና እርምጃዎች ‘ለምን’ የሚለውን
             ጥያቄ አንስቶ ከመመርመር ይልቅ አብዛኞቻችን አንድን የፖለቲካ አመለካከት በጅምላ እና
             በጭፍንነት መደገፍ ይታይብናል። ጥቂቶች የሚጠይቁ ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ ውስብስብ
             የሆነውን  የፖለቲካ  መስተጋብር  ወደ  ጥቂት  የአመክንዮ  ሰበዞች  የማቀናነስ  አዝማሚያ
             (simplification)  ይታይባቸዋል።  እንዲህ  አይነቱ  አዝማሚያዎች  በተለይም  ወጣቱን
             በስሜታዊነት በማነሳሳት አስፈላጊ ወዳልሆነ የእልቂት አዙሪት ሲመሩት ይታያሉ። ባለፉት
             ሰላሳ  ዓመታት  ምንም ዓይነት  ቀጥተኛ  ተሳትፎ ባይኖረኝም፣  ‘ለምን’  የሚለውን ጥያቄ
             ባገኘሁት የተናጠል አጋጣሚ ሁሉ እንደ ዜጋ ማንሳቴ አልቀረም።

                     ከቅርብ  ጊዜ  ወዲህ  በሃገራችን  እየበረታ  የመጣው  የፖለቲካ  ምስቅልቅል
             እያሳሰበኝ በመምጣቱ፣ በዋና ዋና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ምሁራዊ ሃሳቦችን በአዲስ አድማስ
             ጋዜጣ  ላይ  እንዳጋራ  አድርጎኛል።  እነኝህን  ጽሁፎች  የተከታታሉ  እና  በጽሁፎቹ  ላይ
             ተመርኩዞ በጥቂት ሚዲያዎች የቀረቡትን ውይይቶች ያዳመጡ ኢትዮጵያውያን፣ ጽሁፎቹ
             በመጽሀፍ  መልክ  ተደራጅተው  እና  ዳብረው  ቢቀርቡ  አመለካከቱ  በይበልጥ  ለህዝብ፣
             በተለይም  ለወጣቱ  ትውልድ  ተደራሽ  እንዲሆን  ያደርገዋል  የሚል  ሃሳብ  ሰንዝረዋል።
             ይህንን  መሰረት  በማድረግ  የምህዳራዊ  አስተሳሰብ  ታሪካዊ  አመጣጥ  እና  ዋና  ዋና
             እሳቤዎቹን በማቅረብ እና ቀደም ሲል በጋዜጣ የወጡትን ጽሁፎች ይበልጥ በማብራራት
             በመጽሀፍ መልክ ተደራጅቶ ቀርቧል።
                     በዚህ መጽሃፍ ውስጥ የተካተቱ ሃሳቦች በወጣትነት ዘመኔ በነበረኝ የፖለቲካ
             እይታ እና በጎልማሳነት ከኖርኩበት የአካዳሚ እና ዓለም አቀፍ የስራ መስክ በተቀሰሙ
             የሙያ ልምዶች የተቃኙ በመሆናቸው የራሳቸው ውሱንነት እንደሚኖራቸው እገምታለሁ።
             ይህ ውሱንነት እንዳለ ሆኖ፣ በተለይ ወቅቱ ለሚጠይቀው የብሔራዊ መግባባት ውይይት
             የራሱን ድርሻ ያበረክታል የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ በተጨማሪም፣ ወጣቱን ትውልድ
             ዘመኑን ከሚመጥን የዕውቀት መስክ ጋር በመጠኑ በማስተዋወቅ የምክንያታዊ ጠያቂነት
             (critical thinking) ባህልን እንዲያዳብር ያግዛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።






                                                                          5
   8   9   10   11   12   13   14   15   16   17   18