Page 14 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 14

ደስታ መብራቱ


           መግቢያ

                  ዘመናዊው  ፖለቲካ  በኢትዮጵያ  መቀንቀን  ከጀመረበት  ከ1950ዎቹ  ጀምሮ፣
           ሃገራችን  ኢትዮጵያ  እና  ህዝቦቿ  በበርካታ  የፖለቲካ  ውጣ  ውረድ  ውስጥ  አልፈዋል።
           ባለፉት ስልሳ ዓመታት የተፈጠሩ የተለያዩ የፖለቲካ ሁነቶች እና የለውጥ አጋጣሚዎች
           የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ከማስቻል ይልቅ ለበርካታ የሀገሪቱ ዜጎች መሞት
           እና መፈናቀል    ምክንያት ሆነው አልፈዋል። ባለፉት ጥቂት የሽግግር ዓመታትም፣ ይህ
           አሳዛኝ ሁኔታ ተባብሶ ሃገሪቱን ለበለጠ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ አጋልጧታል።
           ውስብስብ የሆነውን ሃገራዊ የፖለቲካ ህመሞቻችንን ባንድ አቅጣጫ በተቀነበበ ትንተና
           ለመረዳት  እና  ቀላል  መፍትሔ  ለመሻት  የሚደረገው  ጥረትም  ችግሩን  በይበልጥ
           እያወሳሰበው በመሄድ ላይ ይገኛል። በነዚህ ሂደት ውስጥ የጉዳቱ ከፍተኛ ገፈት ቀማሽ
           የነበረው  በየዘመኑ  የነበረው  ወጣት  ትውልድ  ሲሆን  ከቅርብ  ጊዜ  ወዲህ  ህጻናት  እና
           ሴቶችም የቀውሱ ቀጥተኛ ተጠቂ እየሆኑ መጥተዋል። የአጠቃላይ ህብረተሰቡም የዕለት
           ተዕለት ኑሮ ከድጡ ወደማጡ እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል።
                  በሃያኛው  ክፍለ  ዘመን  የታየው  እጅግ  ፈጣን  የሳይንስ፣  ቴከኖሎጂ፣  እና
           ኢንዱስትሪ  እድገት  በቢሊዮን  ለሚቆጠሩ  የዓለም  ህዝቦች  ከድህነት  መላቀቅ  መሰረት
           መሆኑ እሙን ነው። በሌላ በኩል ግን ይኸው እድገት ለበርካታ ውስብስብ ኢኮኖሚያዊ፣
           አካባቢያዊ፣ ማህበራዊ፣ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎች ምንጭ ሊሆን ችሏል። ይህም፣ በርካታ
           የዓለማችንን ህዝብ ወደከፋ ድህነት ከመግፋት አንስቶ ለዓለማችን ከፍተኛ ስጋት የሆነውን
           የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት እና የምድራችን ሙቀት መጨመርን ያካትታል። ከዚህ ጎን ለጎን፣
           የዓለማችን ህዝብ ብዛት በብዙ እጥፍ መጨመር ፈተናውን ይበልጥ እያወሳሰበው ነው።
           እነኚህን  ፈተናዎች  በልዩ  ልዩ  የሳይንስ  መስኮች  በተደረጉ  ምርምሮች  ለመረዳት  እና
           ለመፍታት ጥረት ቢደረግም ችግሮቹ ይበልጥ እየተባባሱ እና እየተወሳሰቡ ከመሄድ ሊገቱ
           አልቻሉም።

                  ምህዳራዊ  አሰተሳሰብ  (systems  thinking)  እንዲህ  አይነት  ውስብስብ
           ችግሮችን በአግባቡ ለመረዳት እና መፍትሄ ለመሻት ከ1950ዎቹ ጀምሮ እየዳበረ የመጣ
           የልዕለ-ዘርፍ  (transdisciplinary)  ሳይንስ  ነው።  እንደ  ልዕለ-ዘርፍ  ሳይንስነቱ  የሃያ
           አንደኛው ክፍለ ዘመን ሳይንስ ተብሎ ቢጠቀስም፣ ምህዳራዊ አስተሳሰብ ለማንኛውም
           ሰው በተፈጥሮ ከሚሰጥ ክህሎት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ በመሆኑ ሁላችንም ልናዳብረው
           የምንችለው አስተሳሰብ ነው። ለዚህም ማረጋገጫው፣ ምንም ዓይነት ዘመናዊ ትምህርት
           ሳይኖራቸው እዚሁ በሃገራችን በተለያየ ወቅት ከበርካታ ማህበረሰቦች መሃል ወጥተው
           የነበሩ እና ውስብስብ ማህበራዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮችን ሲፈቱ የኖሩ አስተዋይ ሰዎች
           መኖራቸው ነው። የዚህን አስተሳሰብ መሰረታዊ ይዘት ለመረዳት እንዲረዳ፣ የምህዳራዊ
           አስተሳሰብ  መሰረታዊ  መነሻዎች  እና  መርሆዎች  በመጽሐፉ  የመጀመሪያው  ክፍል
           ቀርበዋል። ይኸው ክፍል፣ ምህዳራዊ አስተሳሰብ ከሃገር በቀል እውቀቶች ጋር ያለውን
           ትስስርም ያሳያል።
   9   10   11   12   13   14   15   16   17   18   19