Page 15 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 15

ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ


                     በመጽሐፉ ሁለተኛው ክፍል፣ ላለፉት ስልሳ ዓመታት በሀገራችን ሰፍኖ የቆየውን
             እና  በአሁኑ  ወቅትም  ያለውን  የፖለቲካ  ህመም  እና  ምስቅልቅል  ዋነኛ  መሰረታዊ
             የአመለካከት  ችግሮች  ከምህዳራዊ  አስተሳሰብ  አኳያ  ለማመላከት  ተሞክሯል።
             በተጨማሪም፣  ዛሬ  ያሉብንን  ዋና  ዋና  የፖለቲካ  መሰረታዊ  ህመሞች  እና  መዋቅራዊ
             ችግሮቻችን  ከምህዳራዊ  አስተሳሰብ  አኳያ  በመተንተን  እነኚህን  ችግሮች  ከምንጫቸው
             ለማድረቅ የሚያስፈልጉንን ዐበይት የአመለካከት ሽግግሮች በማያያዝ ቀርቧል።
                     ከዚህ ቀደም በጋዜጣ ላይ የወጡት ጽሁፎቼ በዋነኝነት ያተኮሩት የሃገሪቱን ዋነኛ
             የፖለቲካ  ጥያቄዎች  ከምህዳራዊ  አስተሳሰብ  አኳያ  በመተንተን  ለፖለቲካ  መሪዎች  እና
             ተንታኞች ጠቋሚ ሃሳቦችን ማቅረብ ላይ ነበር። ሌላው፣ ከፖለቲካዊው ፈተናችን ጋር
             በጥብቅ  የተሳሰረው  እና  ምናልባትም  ለሃገሪቱ  ዘላቂ  ሰላም  እና  ለህዝቡም  ሁለንተናዊ
             ደህንነት (Wellbeing) ከፍተኛ ፈተና የሆነው አብይ ጉዳይ በሃገሪቱ ተንሰራፍቶ የሚገኘው
             የኢኮኖሚ ኋላ ቀርነት እና ድህነት ነው። ይህ ሁኔታ እጅግ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ
             ከመጣው የህዝብ ቁጥር እድገት እና ስራ አጥ ወጣት ቁጥር ጋር ተዳምሮ ዘላቂ ልማት
             ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እጅግ ፈታኝ አድርጎታል።

                     በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እየገነነ የሚመጣው የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጽእኖም
             በማደግ ላይ ያሉ ሃገሮችን የልማት ጥረት ይበልጥ ፈታኝ እንዲሚያደርገው ይጠበቃል።
             ያም ሆኖ ግን፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሃገሮች ሃገራዊውን የተፈጥሮ እና
             የሰው  ሃብት  ከዓለም    አቀፋዊ  እድሎች  ጋር  በብልሃት  እና  በእውቀት  የሚያስተሳስሩ
             ፖሊሲዎች  መተግበር  እስከቻሉ  ድረስ  አካታች  እና  ዘላቂ  ወደሆነ  የኢኮኖሚ  ልማት
             ለመስፈንጠር (leapfrog)  የሚያስችል እድል ይኖራቸዋል። በዚህ መጽሐፍ ሶስተኛው
             ክፍል፣ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫዎች የሚወስኑትን አበይት
             ገፊ ምክንያቶች (drivers) በመተንተን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሃገሮች
             በሚያወጧቸው የኢኮኖሚ  ፖሊሲዎች  ትኩረት  ሊሰጧቸው የሚገቡ  አበይት ነጥቦችን
             ያመላክታል።
                     ምንም እንኳን ይህ መጽሀፍ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ተደራሽ እንዲሆን ቢፈለግም
             በአበይትነት የተጻፈው ግን ለወቅቱ የሃገራችን ፖለቲካ ተዋናዮች እና ለሃገራችን ወጣቶች
             መሆኑን  ለመግለጽ  እፈልጋለሁ።  የዚህ  ዋነኛው  ምክንያት፣  የፖለቲካ  ተዋናዮቻችን
             በአብዛኛው  ወደ  ኋላ  (rear-view  mirror)  እየተመለከቱ  ሃገር  ለመምራት  ከመሞከር
             ይልቅ  ወደፊት  ለመመልከት  የሚያስችላቸው  ግንዛቤ  መስጠት  እና  ወጣቱን  ትውልድ
             በህብረተሰባችን ውስጥ ተንሰራፍተው ካሉ የተዛቡ አመለካከቶች ማላቀቅ ወሳኝ በመሆኑ
             ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የወጣቱ ትውልድ በምህዳራዊ አስተሳሰብ መታነጽ ሃገራችን በሃያ
             አንደኛው ክፍለ ዘመን ለሚያጋጥሟት የኢኮኖሚ፤ ማህበራዊ፣ አካባቢያዊ እና ፖለቲካዊ
             ፈተናዎች የሚኖራትን ዝግጁነት የሚወስን እንደሚሆን በማመን ነው።




                                                                          7
   10   11   12   13   14   15   16   17   18   19   20