Page 19 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 19

ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ


             1.2 ቀውሶች እንደ ዕውቀት ጫሪዎች

                     ታዋቂው የሳይንስ ፍልስፍና ምሁር ቶማስ ኩን (Thomas Kuhn) እንዳለው፣
             ባንድ  ዘመን  ባለ  ዕውቀት  ሊተነተኑ  እና  ሊፈቱ  የማይችሉ  ተደራራቢ  እና  ውስብስብ
             የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ቀውሶች መከሰት የሚያመላክቱት አዲስ እና ዓይነታዊ ለውጥ
             ሊያስከትሉ የሚያስችሉ ሳይንሳዊ አስተሳሰቦች አስፈላጊነትን ነው። ለብዙ ሺህ ዓመታት፣
             የሰው ልጅ በተፈጥሮ አካባቢው ላይ የሚያደርሳቸው ተጽእኖዎች  ባንድ አካባቢ የተወስኑ
             እና  በተፈጥሮአዊው  የማዋሃድ  አቅም  (assimilation  capacity)  ውስጥ  የሚስተናገድ
             ነበር።  ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ የታየው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት
             በምድራችን የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ላይ ያስከተለው ተጽእኖ መጠነ ሰፊ በመሆኑ እና
             ከምድራችን የማዋሃድ አቅም በላይ በመሆኑ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ፈተና ደቅኗል።
             ይህን  ተከትሎ  የተከሰተው  የዓለማችን  ሙቀት  መጨመር  በዓለም  ዙሪያ  የሚከሰቱ
             የተፈጥሮ  አደጋዎችን  በቁጥርም  ሆነ  በጉዳት  መጠናቸው  በክፍተኛ  ደረጃ  እንዲያድጉ
             አድርጓቸዋል።
                     ባለፉት ጥቂት ዓስርተ ዓመታት በሃገራችን በኢትዮጵያ የተከሰቱት እና በብዙ
             መቶ ሺህ ለሚቆጠር የሃገራችን ህዝብ ሞት እና መፈናቀል ምክንያት የሆኑት የድርቅ እና
             ጎርፍ አደጋዎች የዚሁ ዓለም አቀፋዊ ፈተና አካል ናቸው። ኮሮናን ጨምሮ ባለፉት ሃያ
             ዓመታት  ውስጥ  የተከሰቱ  አስር  የወረርሽኝ  በሽታዎችም  በዓለም  ዙሪያ  ከተከናወኑ
             የተፈጥሮ  ደን  መውደም  እና  የብዝሃ  ህይወት  መመናመን  ጋር  በጥብቅ  የተያያዙ
             መሆናቸውን የሚያመላክቱ ሳይንሳዊ መረጃዎች አሉ።

                     ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ የታየው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት
             ያስከተለው  ሌላው  ዐቢይ  መዛባት  ሃገሮች፣  በተለይም  በማደግ  ላይ  ያሉ  ሃገሮች፣
             በኢኮኖሚያቸው ላይ ያላቸውን ሉዓላዊነት የሚያሳጣው ሉላዊነት (globalization) ነው።
             ይህ የኢኮኖሚ ሥርዓት ባራመዳቸው የተዛቡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የተነሳ ባለፉት ሃምሳ
             እና ስልሳ ዐመታት ውስጥ  በሃገሮች ውስጥ እና በሃገሮች መካከል ከፍተኛ የሃብት ልዩነት
             በመፍጠር ዕልፍ ዓዕላፋትን ለከፋ ድህነት እና የኑሮ ጉስቁልና ዳርጓል።  እንደ አውሮፓ
             አቆጣጠር (እ.አ.አ.) በ2016 ኦክስፋም የተባለው ድርጅት ባወጣው ረፖርት መሰረት፣ በ
             2015  (እ.አ.አ.)  በዓለም  ውስጥ  የነበሩት  62  ሃብታሞች  የነበራቸው  የሃብት  መጠን
             በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ 3.6 ቢሊዮን ሰዎች ከነበራቸው አጠቃላይ ሃብት ጋር
             ተመጣጣኝ ነበር። ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ይህ የሃብት መጠን ክፍተት በከፍተኛ
             መጠን እየጨመረ መሄዱን የሚያመላክቱ መረጃዎች በመውጣት ላይ ይገኛሉ።






                                                                        11
   14   15   16   17   18   19   20   21   22   23   24