Page 21 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 21
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
1.3 ፍልስፍናዊ መነሻዎች
በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ፣ እውነትን ፍለጋ (search for truth) የእውቀት
ምንጭ እና የፍልስፍናዎች ሁሉ መሰረት መሆኑ ይነገራል። ይኸው የእውነት ፍለጋ
ያልተገደበ ጉጉት (unbounded curiosity) የሳይንስ ፍልስፍናም መሰረት ሆኖ ዘልቋል።
ከላይ የተዘረዘሩት ተደራራቢ ቀውሶች እየተጠናከሩ እና ይበልጥ ውስብስብ እየሆኑ
መምጣት የሳይንሱ ማህበረሰብ መሰረታዊ የፍልስፍና ጥያቄዎችን እንዲያነሳ
አስገድደውታል። በዚህ ሂደት ውስጥ በርካታ መሰረታዊ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም፣ ከዚህ
መጽሐፍ ጋር በተያያዘ የተወስኑትን ባጭሩ እንመለከታለን። ከዚህ ውስጥ ቀዳሚው
በእውነት አመክንዮ (logic of truth) ዙሪያ የተነሳው ጥያቄ ነበር። በዚህ ረገድ ወደ ኋላ
ያለውን ጥንታዊ ታሪክ መለስ ብለን ስንመለከት የምዕራባውያንን እና የምስራቁን ዓለም
አመክንዮ ታሪክ እናገኛለን፡፡ ይህም፣ በሁለትዮሽ እውነት (bivalent truth) እና በሁለገብ
እውነት (multivalent truth) አመክንዮ ላይ ለተመሰረቱ የሁለት አለሞች ፍልስፍና
መሰረት ሆኖ ዘልቋል። ምንም እንኳን የሳይንስ ዋነኛው ዓላማ እውነታዎችን ወይም
እውነትን መፈለግ መሆኑ በሁሉም የሳይንስ ልሂቃን ቢነገርም እውነት ምንድን ነው
ለሚለው ጥያቄ በሚሰጠው መልስ ላይ ለዘመናት የዘለቀ ልዩነት ነበረ። በምዕራባውያኑ
የፍልስፍስና መርሆዎች መሰረት ማንኛውንም ዕውነታ በጥልቀት ለመረዳት ሁል ጊዜ
በጥቁር እና በነጭ እውነታ ላይ በተመሰረተ የሁለትዮሽ አመክንዮ መተንተን እንደሚገባ
ያምናል። በዚህ ፍልስፍና መሠረት፣ በነዚህ እውነታዎች መካካል ያለውን አእምሮአዊ
መስመር በተሻለ ግልጽ አድርገህ ባወጣህ መጠን አእምሮህም ይበልጥ አመክንዮአዊ፣
ሳይንስህም ትክክለኛ ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል ግን፣ በተለይ በምስራቁ ዓለም ፍልስፍና የተቃኘው የሁለገብ
እውነታ፣ የገሃዱ ዓለም እውነታ ባብዛኛው በግራጫነት የሚታወቅ ሲሆን ጥቁር እና ነጭ
ዕውነት የግራጫውን ዓለም ጊዜያዊ እና ተሸጋጋሪ እውነታ (transient state)
የሚያመላክት ነው ይላል። በዚህም መሰረት ሁለገብ አመክንዮ ሁሉም ሳይንሳዊ እውነቶች
ግራጫ ናቸው ሲል የሁለትዮሽ አመክንዮ ግን በአንድ በኩል ሳይንሳዊ ዕውነቶች ግራጫ
አለመሆናቸውን አበክሮ እየገለጸ በሌላ በኩል የበለጠ መረጃዎች በተገኙ መጠን
ተቀባይነታቸውን የሚያጡ ጊዜያዊ እውነቶች ናቸው ይላል።
በሁለትዮሽ እና ሁለገብ እውነታ አራማጆች መካከል የነበረው ክርክር እና
ፉክክር ለረጅም ዘመን የሁለትዮሽ እውነታ የሳይንሱን ዓለም በበላይነት ይዞ እንዲቆይ
2
አድርጎታል። ሆኖም ግን፣ ከሁለገብ ዕውነታ ጋር የተያያዙ እንደ ኳንተም ፊዚክስ ጽንሰ
ሃሳብ ያሉ ሳይንሳዊ አስተሳሰቦች በሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ከመውጣታቸው ጋር
2 የኳንተም ፊዚክስ መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳብ፣ ማንኛውም በአጽናፈ ሰማይ ውስጥ ያለ ነገር
በተመሳሳይ ጊዜ የጥቃቅን ቁስነት (particle) እና የሞገድነት (wave) ተፈጥሮ አለው ብሎ
ያምናል። ይህም፣ ለረጂም ዘመናት በጥቃቅን ቁስ ወይንም ሞገድ አስተሳሰብ ላይ ተመርኩዞ
የነበረውን የፊዚክስ አስተምህሮ ከመሰረቱ ቀይሮታል።
13