Page 17 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 17

ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ


             1. አካባቢ፣ ሳይንስ እና ምህዳራዊ አስተሳሰብ

             1.1 ሰው እና የተፈጥሮ ምህዳር

                     የሰው  ልጅ  በቀደምት  አናኗሩ፣  እንደማንኛውም  በምድራችን  እንደሚገኙ
             ፍጡራን ህልውናው ባካባቢው በነበረው የተፈጥሮ ምህዳር ሙሉ ቁጥጥር ስር እንደነበር
             ታሪክ እና ሳይንስ ያረጋገጠው ጉዳይ ነው። ያም ሆኖ፣ የሰው ልጅ አካባቢውን ለማወቅ
             እና ለመረዳት ያለውን ልዩ ጉጉት (curiosity) መሰረት በማድረግ በህይወቱ ውስጥ ያሉ
             አበይት ተፈጥሮአዊ ኡደቶችን (natural cycles)  ለመረዳት ሲታትር ቆይቷል። በዚህም
             ጥረቱ፣ ባካባቢው የሚገኙትን የተፈጥሮ ሃብቶች ለህይወቱ ቀጣይነት በሚጠቅም መልኩ
             ክመገልገል ባሻገር በአጥናፈ-ሰማይ (the universe) ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና የኃይል
             እና ኡደት ምንጮችን ለመገንዘብ ሙከራ አድርጓል። ይህንን መነሻ በማድረግም፣ ፀሐይን
             እና  በዙሪያዋ  የሚገኙ  ፕላኔቶችን  በመለየት  ከነርሱ  ጋር  የነበረውን  ግንኙነት  በተለያየ
             መልኩ ለራሱ እንደሚጠቅም አድርጎ ለመቃኘት ሞክሯል። በዓለማችን ቀደምት ከሆኑት
             ሥርወ-መንግሥታት  መካከል፣  የአዝቴክ፣  የማያ፣  የፈርኦን  እና  የአክሱም  ሥርወ-
             መንግሥታት ትተውልን ያለፉት የሥነ ህንጻ ቅሪቶች ይህንኑ የሚያመላክቱ ናቸው። በዚህ
             ሂደት ውስጥ፣  የሰው  ልጅ  ስለአካባቢው  እና  ምድራችን ስለምትገኝበት  አጥናፈ-ሰማይ
             ያለውን ዕውቀት ለማዳበር በመቻሉ ራሱን ከሌሎች ፍጡራን በበለጠ ከተፈጥሮ አካባቢው
             ሊያገኝ የሚችለውን ተጠቃሚነት ሊያጎለብት ችሏል።
                     የዘመናዊው ሳይንስ ዋነኛው መሰረት ከተጣለበት ከአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን
             ሁለተኛው አጋማሽ ጀምሮ ያለው ዘመን በሰው ልጅ የዕውቀት አድማስ ውስጥ እጅግ
             ከፍተኛ የዐይነት ለውጥ የታየበት ዘመን ነው። ይህም፣ ቀደም ሲል በልዩ ልዩ የፍልስፍና
             እና እምነት ዘርፎች ላይ የተመሰረተው የሰው ልጅ ዕውቀት በተለያዩ የሳይንስ መስኮች
             በመደርጀት ይበልጥ ጥልቀት እና ግዝፈት እያገኘ እንዲመጣ አስችሏል። በዚህ ሁሉ ሂደት
             ውስጥ  የተፈጥሮ  አካባቢያችን፣  ለኑሮ  አስፈላጊ  የሆኑ  ግብዓቶችን  ከመስጠት  ባሻገር
             የዕውቀቶቻችን  ሁሉ  ዋነኛ  ምንጭ  በመሆን  አገልግሏል።  በመሆኑም፣  ከዝቅተኛው
             የቴክኖሎጂ  ውጤቶቻችን  እስከ  ከፍተኛው  የዘመናችን  ሰው-ሰራሽ  ብልህነት  (arficial
             intelligence)  ድረስ  ያሉ  የቴክኖሎጂ  ዕውቀቶች  በሙሉ  ተፈጥሮን  በማጥናት  እና
             በማስመሰል (mimcry) ላይ የተመረኮዙ ናቸው። ይህንን፣ በሰው ልጅ የእውቀት አድማስ
             እና  በተፈጥሮ  አካባቢው  መካከል  ያለውን  ጥብቅ  ቁርኝት  አለመረዳት  የሰው  ልጆችን
             በተለያዩ ወቅቶች ለተከሰቱ የመታበይ (hubris) ፈተናዎች እንዲጋለጥ አድረገውታል።
             ይህም፣ ራስን ወደ ፈጣሪነት የማስጠጋት እና የተፈጥሮ አካባቢውን ምህዳራዊ መረጋጋት
             እና ዘላቂነት ከግምት ውስጥ አለማስገባት አስከትሏል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በታሪክ
             ውስጥ ቀደምት የሚባሉት ሥልጣኔዎች እንዲንኮታኮቱ ካደረጓቸው አበይት ምክንያቶች
             አንዱ  መሆኑን  በከባቢያዊ  አርኪኦሎጂ  (Environmental  archaeology)  መስክ
             የተከናወኑ ጥናቶች አመላክተዋል።


                                                                          9
   12   13   14   15   16   17   18   19   20   21   22