Page 12 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 12

ደስታ መብራቱ




           መቅድም

                  የዚህን  መጽሐፍ  ርዕስ  የሚመለከቱ  ፖለቲከኞች  እና  የፖለቲካ  ተንታኞች
           በቀዳሚነት የደራሲውን ማንነት ለማወቅ እንደሚፈልጉ እገምታለሁ፡፡ የሙያ ማንነቴን
           በተመለከተ  የዘመናችን  በይነ-መረብ  ያለብዙ  ድካም  በቂ  መረጃ  እንደሚሰጣቸው
           አምናለሁ። የፖለቲካ ‘የጀርባ ታሪኬን’ በሚመለከት ግን ብዙ እንዳይቸገሩ ስለራሴ በጥቂቱ
           ልግለጽ፡፡  የልጅነት  ዘመኔ  አስተሳሰብ  የተቃኘው  በአብዛኛው  ባካባቢዬ  ከምታዘባቸው
           ማህበራዊ ጭቆናዎች እና በተለያየ ወቅት ከአባቴ ከአቶ መብራቱ በላይ ጋር በማደርጋቸው
           ጭውውቶች  ላይ  የተመሰረቱ  ነበሩ።  ያም  ሆኖ፣  በተማሪው  እንቅስቃሴ  ውስጥ
           ከአጫፋሪነት የዘለለ ድርሻ አልነበረኝም። በ1966 ዓም በወቅቱ ስሙ ናዝሬት በአሁኑ ስሙ
           አዳማ በሚገኘው የአፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። ይህንን
           ተከትሎ  የመጣው  የእድገት  በህብረት  የዕውቀት  እና  የሥራ  ዘመቻ  በወቅቱ  የነበረኝን
           የፖለቲካ አመለካካትም ሆነ አጠቃላይ የህይወት እይታ በመሰረታዊ መልኩ የቀየረ ሁነት
           ነበረ። ከአስራ ሰባት እስክ ሃያ አንድ ዓመት እድሜዬ ድረስ፣        ከወጣት እና የሰራተኛ
           ማህበር መሪነት እስከ ቀበሌ ሊቀመንበርነት እና የክፍለ ሃገር የፖለቲካ ሃላፊነት የደረሰ
           ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ነበረኝ። በነዚሁ ዓመታት ውስጥ፣ በቀዳሚነት በኢትዮጵያ ህዝቦች
           አብዮታዊ  ፓርቲ  (ኢህአፓ)  ተባባሪነት  ሶስት  ጊዜ  እና  በኋላም  በማርክሳዊ  ሌኒናዊ
           ሪቮሉዩሽናዊ ድርጅት (ማሌሪድ) አባልነት ሁለት ጊዜ በአስራ አራት የተለያዩ እስር ቤቶች
           ቆይታ አድርጌአለሁ። በመጨረሻም፣ የአስር ዓመት እስራት ተፈርዶብኝ በ1975 ህዳር ወር
           ‘በምህረት’ እስከተፈታሁበት ጊዜ ድረስ በወህኒ ቤት ታስሬአለሁ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ
           ውስጥ የነበረኝ ንቁ እና ቀጥተኛ ተሳትፎ በዚሁ አብቅቷል ማለት ይቻላል።
                  ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ እኔም አንዳንድ የአሁኑ ዘመን ፖለቲከኞች እና
           ተንታኞች ሊወቅሱት የሚዳዱት የዚያ ትውልድ አባል ነኝ። የዚያ ትውልድ እምነት እና
           ጽናት ዋነኛው ምንጭ በወቅቱ የነበረውን ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ጭቆና እና አድልዎ ‘ለምን’
           ብሎ  መጠየቁ  እና  ሁኔታውን  ለመቀየር  ቆርጦ  መነሳቱ  ነበር።  ከዚህ  ጋር  ተያይዞ
           በየትኛውም ወገን ለተከፈለው መስዋአትነት ታላቅ ክብር አለኝ። በዚያው መጠን ግን፣
           የየራሳችንን ፖለቲካ መሪዎች የሚገባውን ያህል ‘ለምን’ ብለን አለመጠየቃችን ብዙ ዋጋ
           እንዳስከፈለን ይሰማኛል። ምንም እንኳን ሁሉም እስራቶቼ ይህንኑ ጥያቄ ከማንሳቴ ጋር
           የተያያዙ ቢሆንም፣ የዚያ ትውልድ አባል የሆን ሁላችንም በበቂ ሁኔታ ባለመጠየቃችን
           ለተከተለው ቀውስ የየድርሻችንን ኋላፊነት ልንወስድ ይገባል። ከአስር ዓመታት የፖለቲካ
           እና  የእስር  ህይወት  በኋላ፣  በ1966  ወዳቆምኩት  ትምህርት  በመመለስ  የኬሚካል፣
           ኢንዱስትሪ እና አካባቢ ምህንድስናን በማጥናት ላለፉት ሰላሳ ሁለት ዓመታት ለተለያዩ
           ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎች ስሰራ ቆይቻለሁ።
   7   8   9   10   11   12   13   14   15   16   17