Page 39 - Ayinie Magazine
P. 39
ግጥም
ለሰው መድረስ!
ወጋየሁ ፈጠነ
የብሌን ንቅለ ተከላ የተደረገለት ወጣት
ተስፋን የናፈቀ - ፍቅርን የተጠማ
ዕንባው ያልደረቀ - ትንሳዔን ያልሰማ
ቅኝቱ ምን ይሆን - የወገኔ ዜማ፤
ቅኝቱማ እንደሰው - ኩራትን ተላብሶ
የርቀት ውጥኑ - እንዳይቀር ደፍርሶ
መኖር ህልሙ ነዋ - ጎጆውን ቀልሶ
ከወጋ ወጉ ስር - ከተራራው ደርሶ፡፡
አትፍራ ተራመድ - ጉልበትህም አይዛል
ህልም አለህ እሚፈታ - ጥሪህ ሰሚ አግኝቷል
ሩቅ ትደርሳለህ - ቁጭትህ አብቅቷል፤
ላንተ ዘብ የቆሙት - የአብራኮችህ ክፋይ
ልግስናቸውም - በአደባባይ ሊታይ
ይኸው ተሰየሙ - በክብር መዝገብ ላይ፤
ራዕይ አንግበው - ተስፋን የሰነቁ
በምርምራቸው - ሳይንስን ያወቁ
በወግ ማዕረጋቸው - ለሀገር የበቁ
ቁስልህ አመማቸው - ላንተ ተጨነቁ
ጤና ቢነሳቸው - ጤናህ መታወኩ
በሙያቸው ጥረው - በደስታህ ባይረኩ
አዲስ ብስራት ይዘው - በርህን አንኳኩ
የጨለመብህን - ብርሃን ሊተኩ፤
ይኸው ተሰለፉ - ብሌን ሊለግሱ
አንድ ሆነው እያለ - ሁለቴ ሊደርሱ፤
ይህ ሀቅ ሲመዘን - ይህ እውነት ሲለካ
ሀኪም መሆን ማለት
ዕድሜ ዘላለምን
ለሰው አለሁ ማለት - ፊት መሆን ነው ለካ!!!