Page 8 - Aluma-Amaranthus for design 26.04.14
P. 8
2
ፖታስየም፣ ዚንክ፣ መዳብ እና ማንጋኒዝ የመሳሰሉ የማዕድን የምግብ ንጥረ-ነገሮችን ይዟል። ይህ ሰብል ቅጠሉ
በብረት ማዕድን የበለፀገ በመሆኑ ደም ማነስ ላለባቸው ሰዎች እንዲመገቡት ይመከራል። በተጨማሪም ከፍተኛ
መጠን ያለው ቫይታሚን ኤ ስላለው፤ መቶ ግራም ያለው ያለዘይት የበሰለ ቅጠል በየቀኑ እስከ 45% የእለት
የቫይታሚን ኤ ፍላጎት ያሟላል። የአሉማ እህል (Grain) ፕሮቲን (16-20%)፣ ዘይት (5-10%)፣ ፎስፈረስ፣
ማግኒዥየም፣ ካልሲየም፣ ብረት እና ዚንክ፣ ቫይታሚኖች (ቢ፣ ሲ እና ኢ) እና አሰር (dietary fiber) በውስጡ
ይዟል። በአሉማ እህል ውስጥ ሰውነት ለአጥንት እድገት የሚፈልገውን ካልሲየም ለመጠቀም እንዲችል አስፈላጊ
የሆነውን እና እንደ በቆሎ፣ ሩዝና ስንዴ ባሉ ሰብሎች ውስጥ ግን በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን ላይሲን (lysine)
አሚኖ አሲድ የበለፀገ መሆኑ ከነዚህ አይነት የሰብል አይነቶች ጋር ቀላቅሎ በማዘጋጅት መመገብ የምግቡን የምግብ
ንጥረ ነገር በከፍተኛ ደረጃ ያሻሽላል፡፡
በሀገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በምግብ ዕጥረት እና በአመጋገብ ሂደት ዝቅተኛ የምግብ ንጥረ ይዘት
ያላቸውን ሰብሎች በመመገብ ስር የሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት (Malnutrition) ተጋላጭ ሆኗል፡፡ ይሁንና
የአሉማ ሰብል በቅጠልና በፍሬው ውስጥ ባለው ከፍተኛ የንጥረ ነገር ይዘት፣ ለተለያዩ ቦታዎች በቀላሉ መብቀሉና
አነስተኛ ግብዓት የሚፈልግ በመሆኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። የአሉማ ሰብል ምርታማነት
እንደ ዝርያው አይነት፣ የአመራረት ዘዴና ስነ-ምህዳር የተለያየ ሲሆን፤ በተለያዩ አከባቢዎች የተደረጉ ጥናቶች
እንደሚያሳዩት የአሉማ ለጋ ቅጠል ምርታማነት በሄክታር ከ17 እስከ 40 ቶን ይደርሳል። በሀገራችን የአሉማ
ሰብልን ማምረት እምብዛም ባይታወቅም፤ በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በሄክታር ከ14 እስከ
17.5 ቶን ለጋ ቅጠሎችን ማማረት ይቻላል። በአብዛኛዉ በቤት አካባቢ የሚመረትና በአነስተኛ ቦታ ከፍተኛ ምርት
የሚሰጥ በመሆኑ ለሴቶች የስራ እድልን ከመፍጠር አንፃር ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
በሀገር ደረጃ የአሉማ ሰብል በምርምር እና ልማት ውስጥ ከዚህ በፊት ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ ቢሆንም በአሁኑ
ወቅት ግን ሰብሉ ለምግብና ስርዓተ ምግብ ዋስትና መረጋገጥ ያለውን እምቅ አቅም በመረዳት የምርምር ተቋም
ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከውጭ ሀገር ሁለት ዝርያዎችን አስገብቶ በማላመድ በሀገራችን ሁለት
ዝርያዎች እንዲመዘገቡ ተደርጓል:፡ በመሆኑም ለግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤ ይዘው አምራቾችን
በሚፈለገው መልኩ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዲችሉ ታሳቢ በማድረግ ይህን ፓኬጅ ማዘጋጀት አስፈልጓል።
በዚህ ፓኬጅ ውስጥ ሰብሉን ለማምረት ምቹ የሆኑ ስነምህዳር፣ የተለቀቁ ዝርያዎች፣ የተሻሻሉ የአመራረት
ዘዴዎች፣ ሰብል ጥበቃ፣ ምርት አሰባሰብ እና ድህረ-ምርት አያያዝ እንዲሁም ምርቱ ለምግብነት እንዴት ጥቅም ላይ
እንደሚውል የሀገር ውስጥና የሌሎች ሀገሮችንም ልምድ ይዞ ቀርቧል።
የአሉማ (Amaranthus spp.) ሰብል አመራረት እና አጠቃቀም ፓኬ ጅ
የአሉማ (Amaranthus spp.) ሰብል አመራረት እና አጠቃቀም ፓኬጅ