Page 100 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 100
ደስታ መብራቱ
7. አካታች እና ዘላቂ ልማት
በአንድ ሃገር የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሥርዓት መካከል ጥብቅ ትስስር መኖሩ
በዘርፉ ቀደምት ነው ከሚባለው ከካርል ማርክስ ጀምሮ የነበሩ ዕውቅ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ
ምሁራን አበክረው ያስገነዘቡት ጉዳይ ነው። ከዚህም የተነሳ፣ ባንድ ሃገር የፖለቲካ ሁኔታ
ላይ የሚደረግ የፖለቲካ ምልከታ ኢኖሚውን ሳያካትት የተሟላ ሊሆን አይችልም። በ
1950ዎቹ የተጀመረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ የተሟላ የፖለቲካ ንቅናቄ መሆን
የቻለውም የባላባታዊው ሥርዓት መሰረት የነበረውን የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ካነሳበት ጊዜ
ጀምሮ ነው። የ1967 የመሬት አዋጅ ይህንን መሰረታዊ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ጥያቄ ከመለሰ
ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እጅግ ገኖ የሚታየው የዲሞክራሲ እና የስልጣን ጥያቄ
ሆኖ ቆይቷል። ይህም፣ ከነበረው የገዘፈ የዲሞክራሲ ረሃብ እና የመብት ጥሰት አኳያ ተገቢ
ነበር ማለት ይቻላል። ያም ሆኖ፣ በተከታታይ መንግሥታት ይወጡ የነበሩ የኢኮኖሚ
ልማት ፖሊሲዎች እና እቅዶች በየወቅቱ ለነበረው የፖለቲካ ችግር መባባስ ከፍተኛ
አስተዋጽኦ ማድረጋቸው አይካድም። በቅርቡ የነበረውን የኢህአዴግ ዘመን የኢኮኖሚ
ፖሊሲ እንኳን ብንመለከት በዋነኝነት በስልጣን ላይ ያለው ቡድን የፖለቲካ ዓላማ
አገልጋይ እንዲሆን ተደርጎ በመቀረጹ እና በመተግበሩ የሥርዓቱን ተጠቃሚዎች ይበልጥ
ሲያበለጽግ የአብዛኛውን ህዝብ የኑሮ መከራ አባብሶታል። በዚህም የተነሳ፣ የበርካታ
ሚሊዮን ህዝቦች ህይወት ከመመሰቃቀሉም ባሻገር ፖለቲካዊ መስተጋብሩንም ይበልጥ
ሲያወሳስበው ታይቷል። በመሆኑም፣ ኢትዮጵያን ለማሻገር የሚደረገው ጥረት ፖለቲካውን
ከኢኮኖሚው ጋር አስተሳስሮ መመልከት ይጠይቃል።
የማንኛውም ዴሞክራሲያዊ መንግስት ታላቁ ፈተና የህዝቦቻቸውን መሰረታዊ
ፍላጎት ለማሟላት እና ዘላቂ ደህንነታቸውን (wellbeing) ለማረጋገጥ የሚያስችል
የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት ነው። እንዳለመታደል ሆኖ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ
የአፍሪካ ሀገራት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትም ሆነ መሰረታዊ የህዝቦችን ፍላጎት
የሚያሟላ የኢኮኖሚ ሥርዓት መፍጠር ተቸግረው ኖረዋል። እስካሁን ድረስ ለዘለቀው
ኋላ ቀርነታችን ምንጮች እና ለተደረጉ የልማት ጥረቶች ሁሉ መክሸፍ ዋነኛ ምክንያቶችን
በተመለከተ፣ በርካታ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አጥኚዎች እና ተንታኞች
የየራሳቸውን ምክንያቶች እና መላ ምቶች ሲሰነዝሩ ኖረዋል። የዚህ ክፍል ዋና ዓላማ፣ ዛሬ
ሃገራችን ከምትገኝበት አሳፋሪ የድህነት ደረጃ ለመውጣት እንዴት አካታች እና ዘላቂ ልማት
ለማምጣት እንችላለን የሚለውን ለማመላከት ነው። በሃገራችን ውስጥ ልናየው የምንሻውን
የኢኮኖሚ ልማት እና እድገት ለማምጣት፣ በዓለም አቀፋዊውም ሆነ በሃገራችን ደረጃ
ያሉብንን ዋና ዋና ፈተናዎችን እና እድሎችን በጥልቀት መረዳት የመጀመሪያው ተግባር
መሆን ይኖርበታል። በዚህ ላይ ተመርኩዞም በፈተናዎቹ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት
መቀነስ ወይንም ማስቀረት እና እድሎቹንም በተቻለ መጠን ለመጠቀም የሚያስችሉ
ፖሊሲዊችን መንደፍ እና መተግበር ይጠይቃል።