Page 101 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 101
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
7.1 አጠቃላይ የልማት እና ዕድገት ፈተናዎች
ዛሬ ባለው እጅግ የተሳሰረ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ፣ ያንድን ሃገር የልማት
እና ዕድገት ፈተናዎች ከዓለም አቀፋዊው ሁኔታ ነጥሎ ማየት የማይቻል ነው። በመሆኑም፣
አብዛኞቹ በማደግ ላይ ያሉ ሃገሮች ዋነኛ የልማት እና ዕድገት ፈተናዎቻቸው በዓለም አቀፍ
ደረጃ ከሚታዩ አበይት ፈተናዎች ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው። ስለዚህም፣ በቀዳሚነት
አሁን በምንገኝበት ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በማንኛውም ሃገር የኢኮኖሚ እድገት እና
ልማት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖዎች ሊያሳድሩ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱትን ዓለም አቀፋዊ
ወሳኝ ክስተቶች ከሃገራችን ልዩ ሁኔታ ጋር አዛምደን በመመልከት እንጀምራለን። በዚህ
ረገድ፣ ምንም እንኳን በርካታ ጉዳዮች ሊነሱ ቢችሉም፣ በዚህ ፀሃፊ እምነት አካታች እና
ዘላቂ ልማትን ሊያደናቅፉ ከሚችሉ ፈተናዎች መካከል የሚከተሉት ዋነኞቹ ናቸው።
የዓለም ሙቀት መጨመር (Global warming)፡ በሃያኛው ክፍለ ዘመን
ለተመዘገበው እጅግ ፈጣን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት
የቴክኖሎጂ ለውጦች አንዱ ታዳሽ ባልሆኑ የኃይል ምንጮች አጠቃቀም ላይ የታየው
ከፍተኛ እድገት ነው። ከዚህ ውስጥ ዋነኛው የችግር ምንጭ፣ ከፋብሪካዎች እና የመጓጓዧ
አገልግሎት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ፍጆታው በከፍተኛ ደረጃ የጨመረው የቅሪተ አካላት
ነዳጅ (fossil fuels) አጠቃቀም ነው። ይህም፣ በከባቢ አየር ውስጥ ሊኖር የሚገባውን
የካርቦን ጭስ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር በማድረጉ የተነሳ የዓለማችንን የሙቀት
መጠን መጨመርን አስከትሏል። በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ የሳይንቲስቶች
(International Panel on Climate Change) ቡድን ጥናት መሰረት፣ የዓለማችን ሙቀት
መጠን በቅድመ ኢንዱስትሪ አብዮት ከነበረው በሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከጨመረ
ተመልሶ ሊተካ የማይችል (irreversible) ከፍተኛ የተፈጥሮ አካባቢ ውድመት ሊያደርስ
እንደሚችል ተረጋግጧል። በ2008 በፓሪስ ከተማ በተደረገው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት
ለውጥ ((climate change) ስምምነት አማካኝነት፣ በአሁኑ ወቅት፣ መላው የዓለም
ህብረተሰብ እንዲህ አይነቱ ጥፋት እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
ይህ ጥረት እንዳለ ሆኖ፣ እስካሁን ድረስ በተፈጠረው የዓለም የከባቢ አየር ሙቀት
መጨመር የተነሳ ሃገራችንን ጨምሮ በርካታ ሃገሮች ተለዋዋጭ ለሆነ የከባቢ አየር ሁኔታ
መለዋወጥ (climate variability) በመጋለጥ ላይ ይገኛሉ። ለዚህም፣ በቅርቡ በሃገራችን
የተከሰቱትን የጎርፍ እና የድርቅ አደጋዎች መመልከቱ በቂ ማረጋገጫ ነው።
የአሜሪካኑን ብሔራዊ የበረራ እና የሕዋ አስተዳደርን (National Aeronautics
and Space Administration) ጨምሮ በርካታ የሳይንስ ጥናት ማዕከሎች እንዳመላከቱት
ከሆነ፣ በመጪዎቹ አስርተ ዓመታቶች እነኚህ የተፈጥሮ አደጋዎች በድግግሞሽ መጠንም
ሆነ በሚያስከትሉት ጉዳት ይበልጥ ጠንካራ እየሆኑ ሊሄዱ እንደሚችሉ ተገምቷል። ምንም
እንኳን እስክ ዛሬ ድረስ ላለው የዓለም ሙቀት መጨመር ችግር የነበራቸው አስተዋጽኦ
ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ይህ ሁኔታ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ የሚገኙ ሃገሮችን ይበልጥ
የጉዳቱ ተጠቂ ከማድረጉም በላይ የልማት ጥረታቸውንም ይበልጥ ፈታኝ
93