Page 103 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 103
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
ወደ ለም አካባቢ መነቃነቅ (mobility) ዛሬም ቢሆን ከተፈጥሮ አካባቢ ጋር ጥብቅ ቁርኝት
ባላቸው ማህበረሰቦች የሚተገበር ዑደት ነው። ይህ ዑደት፣ ዛሬ ያለውን የዓለማችንን
የህዝቦች አሰፋፈር ገጽታ ሊሰጠን ችሏል።
የሁለተኛው ምዕራፍ ዋነኛው መለያ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ከመነቃነቅ
ይልቅ በዕውቀት ላይ የተመረኮዙ ግብአቶችን (intensification) በመጠቀም ከአንድ
የተፈጥሮ ምህዳር ሊገኝ የሚችለውን ምርት ማሳደግ እና እጥረትን እና መመናመንን
መቋቋም ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም የተገኘው የተሻለ ምርት እና የአኗኗር ዘይቤ መቀየር
ለመጀሪያው ዙር የህዝብ ብዛት እድገት አስተዋጽኦ አድርጓል። ከኢንዱስትሪ አብዮት ጋር
ተያይዞም የዓለማችን የህዝብ ብዛት በከፍተኛ መጠን አድጓል። በተለይም ከሃያኛው ክፍለ
ዘመን መጀመሪያ አንስቶ የዓለማችን የህዝብ ብዛት በብዙ እጥፍ አድጎ እ.አ.አ. በ2019 7.7
ቢሊዮን ሲደርስ፣ ይኽው ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2030 8.5 ቢሊዮን እንዲሁም እ.አ.አ. በ2050
ወደ 9.7 ቢሊዮን እንደሚደርስ ተገምቷል። በተመሳሳዩ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት እ.አ.አ.
በ 2017፣ 105 ሚሊዮን እንደነበረ የሚገመት ሲሆን፣ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ 2050 190
ሚሊዮን እና እ.አ.አ. በ 2100 ደግሞ 250 ሚሊዮን እንደሚደርስ ተገምቷል። ይህንን
ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እድገት ግምት ውስጥ ያስገባ የልማት ራዕይ ማበልጸግ የሃገሪቱን
ልማት ዘላቂነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት (Fourth industrial revolution-4IR)፡
የሰው ልጅ የመጀመሪያውን የአደን መሳሪያ ከፈጠረበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ የቴክኖሎጂ
መሳሪያዎችን በመፍጠር የራሱን ህይወት እና አካባቢውን ሲቀይር መጥቷል። በተለይም፣
የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ አብዮት መሰረት የሆነው የእንፋሎት ሞተር (steam engine)
ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ዐለማችንን በተለያዩ ሁለት ተከታታይ የኢንዱስትሪ አብዮቶች
ውስጥ ያሳለፉ ቁልፍ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ነበሩ። አሳዛኙ እውነታ፣ ሃገራችን ኢትዮጵያን
ጨምሮ በርካታ በማደግ ላይ የሚገኙ ሃገሮች ያለፉት ሶስት የኢንዱስትሪ አብዮቶች
በተሳታፊነት ሳይሆን በበዪ ተመልካችነት ማሳለፋቸው ነው።
በአሁኑ ወቅት ዓለማችን የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ዋነኛ መለያ ወደሆነው
አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት በመገስገስ ላይ ይገኛል። የዚህም ዋነኛው መሪ ኃይል
በመረጃ እና ተግባቦት (information and communication) ዘርፍ እየተካሄደ ያለው
እጅግ ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት ነው። ይህ ፈጣን እድገት እስካሁን ድረስ የነበረውን
የአመራረት እና የፍጆታ (production and consumption) አደረጃጀት በመሰረታዊ
መልኩ ሊቀይረው እንደሚችል ይገመታል። ከዚህ ጋር ተያይዞም፣ ለሁሉም ሃገሮች በርካታ
ፈተናዎች እና እድሎችን ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል። ከመልካም ገጽታዎቹ አንዱ፣
አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ባለው ልዩ መረጃን እና ዕውቀትን ለሁሉም ተደራሽ
(democratize) የማድረግ አቅሙ የተነሳ ቀደም ሲል ከነበሩት የኢንዱስትሪ አብዮቶች
በተለየ መልኩ ለሁሉም ሃገሮች የተሻለ ተጠቃሚነት በር መክፈቱ ነው።
95