Page 106 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 106

ደስታ መብራቱ


                       36
                 ‘የሽመና’   እቅድ  (discusiive  planning)፡  ከላይ  ለተጠቀሰው  ‘ምትሃታዊ
           የኢኮኖሚ  ፖሊሲ’  አንዱ  መገለጫው  ተግባራዊነታቸው  በአብዛኛው  አጠያያቂ  የሆኑ
           ዓመታዊ፣ የአምስት ዐመት እና አንዳንድ ጊዜም የአስር ዓመት እቅድ የሚመስሉ ‘ያልታቀዱ
           እቅዶችን’ (unplanned planning) ማውጣታቸው ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የብዙ
           የአፍሪካ ሃገሮች ከፍተኛ የልማት ፈተና አብዛኛውን የሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በእርዳታ
           የሚገኝ  ሃብት  ባግባቡ  ባልታቀዱ  ‘የልማት’  እቅዶች  አማካይነት  ስራ  ላይ  በማዋል
           የሚፈጥሩት  የሃብት  ብክነት  ነው።  ለዚህም፣  በሥልጣን  ላይ  ያለው  ቡድን  አስቦበት
           የተወሰኑ  የፖለቲካ  ቡድን  አባሎችን  እና  ደጋፊ  ወገኖችን  ለመጥቀም  ከሚፈጽማቸው
           ተግባራት  ባሻገር  የሚከተሉት  ሁለት  ችግሮች  በአበይት  ምክንያትነት  ይጠቀሳሉ።
           የመጀመሪያው፣ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታም ሆነ የህዝብን መሰረታዊ ፍላጎት
           ባላካተተ መልኩ ከላይ ወደ ታች በሚወርድ እቅድ (top-down planning) አማካይነት
           ልማትን ለማምጣት መሞከር ነው። ለዚህም፣ እዚሁ በሃገራችን በርካታ መክነው የቀሩ
           ወይንም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ያላመጡ የልማት ፕሮጀክቶችን መዘርዘር ይቻላል።

                 ሁለተኛው ያልታቀደ ዕቅድ ችግር የሚመነጨው በተለያዩ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች
           በሚወጡ  እርስ  በእርስ  ባልተናበቡ  እና  ባልተቀናጁ  (fragmented)  የልማት  እቅዶች
           ምክንያት  የሚፈጠር  የሀብት  ብክነት  እና  ውድመት  ችግር  ነው።  ይህ፣  በተለይም
           የከተሞችን እና የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ለመገንባት በሚወጡ እቅዶች ላይ ጎልቶ
           የሚታይ ችግር ነው። እነኚህን ችግሮች ለማወስገድ፣ ከላይ ወደ ታች የሚወርድ አመላካች
           ዕቅድን  (indicative  planning)  ከታች  ወደላይ  ከሚመግብ  እና  ህዝብን  ካካተተ
           የአፈጻጸም ዕቅድ (operational planning) ጋር ማዋሃድ አካታች እና ዘላቂ የሆነ ልማት
           ለማውጣት እጅግ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የዕቅድ አወጣጥ እና አፈጻጸም ‘የሽመና
           እቅድ’ (discusrive planning) ተብሎ ይታወቃል።

                 ዘላቂ  የልማት  አስተዳደር  (sustainable  development  governance):
           አጠቃላይ  የመልካም  አስተዳደር  (good  governance)  እጦት፣  ኢትዮጵያን  ጨምሮ፣
           የብዙዎቹ  በማደግ  ላይ  ያሉ  ሃገሮች  ችግር  መሆኑ  ተደጋግሞ  የተነገረ  ነው።  ይህንን
           የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታትም፣ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት እና
           የህግ የበላይነትን ማስከበር እንደ ዋነኛ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተደርገው ይጠቆማሉ።
           ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አካታች እና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት ተጨማሪ የልማት መልካም
           አስተዳደር  እርምጃዎችን  መመልከት  ተገቢ  ይሆናል።  ለዚህም  የመጀመሪያው  መነሻ፣
           የሃገሪቱ  የልማት  ጥረት  መሰረታዊ  ግብ፣  ጥቅል  ሃገራዊ  ምርትን  (Gross  Doemstic
           Product (GDP)) እና የነፍስ ወከፍ ገቢን (per capita income) ከማሳደግ ባሻገር፣
           የህዝቦችን ሁለንተናዊ የኑሮ ሁለንተናዊ ደህንነት (wellbeing) ማረጋገጥ ሊሆን ይገባዋል።


           36  የሽመና ስራ ድር እና ማጉን አንዴ ወደ ላይ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደታች በሚደረግ የማያቋርጥ
           እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ በማስተሳሰር ያማረ ሸማ ወይንም ጥበብ እንደሚያወጣው ሁሉ
           discusrive ለሚለው የእግሊዝኛ ቃል የሚመጥን ሆኖ ተገኝቷል።
   101   102   103   104   105   106   107   108   109   110   111