Page 109 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 109

ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ


             7.3 የዘላቂ ልማት ዕድሎቻችን
                     ቀደም ሲል በነበረው ክፍል ለማሳየት እንደተሞከረው፣ በሃያ አንደኛው ክፍለ
             ዘመን  ውስጥ  ዓለማችን  በርካታ  ውስብስብ  እና  ተደራራቢ  የኢኮኖሚ፣  ማህበራዊ፣
             አካባቢያዊ  እና  ፖለቲካዊ  ፈተናዎች  በመጋፈጥ  ላይ  ትገኛለች።  እንደ  ኢትዮጵያ  ያሉ
             በማደግ  ላይ  የሚገኙ  ሃገሮች፣  የእነኚህ  ዓለም  አቀፍ  ፈተናዎች  ዋነኛ  ገፈት  ቀማሾች
             እንደሚሆኑ ይገመታል። በሌላ በኩል ግን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሃገሮች
             ያሉበትን ልዩ  አስቸጋሪ ሁኔታ ወደ መልካም አጋጣሚዎች እና ዕድሎች (opportunities)
             ለመቀየር  የሚችሉበት  ሁኔታ  አሏቸው።  በዚህ  ክፍል  ውስጥ፣  ከነዚህ  መልካም
             አጋጣሚዎች በተለይ ለአካታች እና ዘላቂ ልማት አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉትን ዋና ዋናዎቹን
             ለመመልከት እንሞክራለን።

                     ተፈጥሮአዊ  የማገገም  አቅም  (natural  resilience)፡  በ2020  የተባበሩት
             መንግሥታት ሰብዓዊ ልማት ሪፖርት እንደተመለከተው፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ ያላትን ህያው
             የተፈጥሮ  ሃብት  አቅም  (bio  capacity)  ሙሉ  በሙሉ  የተጠቀመችበት  ደረጃ  ላይ
             ደርሳለች።  ይህም፣  እስከዛሬ  በመጣንበት  የአመራረት  እና  የፍጆታ  (production  and
             consumption) ሥርዓት ከቀጠልን ዋናውን የተፈጥሮ ሃብት ካፒታላችንን እያመናመን
                                                                    37
             የራሳችንንም ሆነ የተተኪውን ትውልድ የኑሮ ዋስትና እናወድማለን ማለት ነው ። በሌላ
             በኩል  ግን፣  ኢትዮጵያ  ሃገራችን  በዓለም  ውስጥ  ከሚገኙ  በጣም  ጥቂት  ከፍተኛ
             የተፈጥሮአዊ ምህዳር፣ የእንስሳት እና የዕፅዋት ሃብት ብዝሃነት ከሚታይባቸው ሃገሮች
             ውስጥ ትመደባለች። እንዲህ ዓይነቱ ዘርፈ ብዙ የሆነ የብዝሃነት ሃብት የሃገሪቱ የተፈጥሮ
             ሃብት መሰረት ከፍተኛ የማገገም አቅም (resilience) እንዲኖረው ያደርገዋል። ለዚህም
             ማረጋገጫው፣ ከዚህ በፊት ሙሉ ለሙሉ ጠፍተው ወይንም ተራቁተው የነበሩ የተፈጥሮ
             ምህዳሮች ተገቢው ትኩረት ሲሰጣቸው እና እንክብካቤ ሲደረግላቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ
             ተመልሰው የቀድሞ ገጽታቸውን መያዛቸው ነው።

                     ስለዚህም፣ የማናቸውም የልማት ፍላጎታችን መሟላት ዋነኛ መሰረት የሆነውን
             የተፈጥሮ  አካባቢያችንን  መንከባከብ  እና  ማልማት  ከህጻንነት  ጀምሮ  የማንኛውም
             ኢትዮጵያዊ ዜጋ ባህል እንዲሆን ማድረግ የሁሉንም ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አካታች
             እና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ዋነኛው ዋስትናችን ነው። ይህንን በማድረግም፣ ቁጥሩ እጅግ
             እያደገ  የሚሄደውን  ህዝብ  የምግብ  ዋስትና  ከማረጋገጥም  በላይ፣  በተለይ  በገጠር
             ተንሰራፍቶ ያለውን ድህነት ለመቀነስ ከፍተኛ መሰረት ይሆናል።





             37  በሌላ አገላለጽ፣ ቋሚ ንብረት ላይ እና ባንክ ውስጥ ቆጥበን ያስቀመጥነው ካፒታል በሚሰጠን
             ትርፍ እና ወለድ ከመኖር ይልቅ ዋናውን ካፒታል እየበላን የኑሮ ዋስትናችንን እናጣለን ማለት
             ነው።
                                                                       101
   104   105   106   107   108   109   110   111   112   113   114