Page 107 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 107
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
ከዚህ በተጨማሪም፣ በአንድ ሃገር ህዝብ ውስጥ ያለውን የማህበራዊ ንዋይ
(social capital) መሰረት በጥልቀት መረዳት እና ይህንንም ባግባቡ ለማነቃነቅ እና
ለመጠቀም መቻል እንደዋነኛ የልማት አካሄድ መተግበር ያስፈልጋል። ይህንን
ለማድረግም፣ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ የሃገር በቀል እውቀቶችን እና የስውሩ ኢኮኖሚ
(informal economy) አሰራሮችን ከነተያያዥ መረቦቻቸው (networks) መረዳት እና
ለልማት ማነቃነቅ ይጠይቃል።
እንዲህ ዓይነቱ የልማት አስተዳደር፣ በተወሰኑ ከተሞች አካባቢ ከሚከማቹ
የኢንዱስትሪ እና ልማት ማዕከሎች ባሻገር ለበርካቶች የስራ ዕድል እና የኑሮ ዋስትና ሊሰጡ
የሚችሉ እና ከየአካባቢው የተፈጥሮ ሃብት እና መሰረታዊ ፍላጎት ጋር የተስማሙ፣
ያልተከማቹ፣ ነገር ግን እርስ በእርስ የተሳሰሩ የኢኮኖሚ መረቦች (distributed economy
networks) እንዲስፋፉ ያደርጋል። ይህንን በማድረግም፣ ፍትሃዊ የሆነ የልማት
ተደራሽነትን ከማረጋገጥም በላይ በየአካባቢው ባለ የተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚደርሱ የልማት
ተጽእኖዎችን ባካባቢው የተፈጥሮ ሃብት የመሸከም እና የማዋሃድ አቅም (carrying and
assimilation capacity) ክልል እንዲስተናገድ ማድረግ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪም፣
በበርካታ የአፍሪካ ሀገሮች እንደሚታየው፣ በከፍተኛ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ተገንብተው
ከአካባቢያዊም (local) ሆነ ከብሔራዊ ኢኮኖሚ ጋር በጣም ዝቅተኛ ትስስር ያላቸው
የውጭ ኢንቬስተር ግዛቶች (enclaves) ሊያደርሱት የሚችሉትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ
እና አካባቢያዊ ጉዳቶች መቀነስ ያስችላል።
ዘመነኛ ክህሎት (skill-sets) ማዳበር፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ የሃያ
አንደኛው ክፍለ ዘመን ኢኮኖሚ ዋነኛው መለያ ከምንጊዜውም በላይ በዕውቀት እና መረጃ
የበላይነት የሚወሰን መሆኑ ነው። በእንዲህ ዓይነት ኢኮኖሚ ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት
ለዘመኑ የሚመጥን ክህሎትን ያለማቋረጥ ማዳበር እና ማበልጸግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ፣
የሚከተሉትን አበይት ነጥቦች መስረት በማድረግ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት በእጅጉ
ሊፈተሽ እና ሊሻሻል ይገባዋል። የመጀመሪያው፣ ከአፀደ ህፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ባሉ
ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚያልፉ ተማሪዎች አካባቢያቸውን በደንብ እንዲረዱ እና
የምክንያታዊነት አስተሳሰብን (critical thinking) እንዲያዳብሩ የሚያስችል የትምህርት
አሰጣጥ ሥርዓትን መተግበር ነው። ይህንን ተመርኩዞም፣ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች
ውስብስብ ችግሮችን በልዕለ-ዘርፍ ሳይንስ ዘዴ (transdisciplinary methodlogy)
ተንትኖ ለመረዳት እና በምህዳራዊ አስተሳሰብ (systems thinking) ላይ የተመረኮዙ
መፍትሔዎችን ለማፍለቅ የሚያስችላቸውን ክህሎት እንዲያዳብሩ ማድረግ ተገቢ ነው።
99