Page 112 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 112

ደስታ መብራቱ


           የክፍል ሰባት ቁልፍ ሐሳቦች
              i.   በአንድ ሃገር የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሥርዓት መካከል ጥብቅ ትስስር መኖሩ
                  በዘርፉ  ቀደምት ከሚባለው ከካርል  ማርክስ  ጀምሮ  የነበሩ  ዕውቅ  የፖለቲካዊ
                  ኢኮኖሚ ምሁራን አበክረው ያስገነዘቡት ጉዳይ ነው። ከዚህም የተነሳ፣ ባንድ ሃገር
                  የፖለቲካ  ሁኔታ  ላይ  የሚደረግ  የፖለቲካ  ምልከታ  ኢኮኖሚውን  ሳያካትት
                  የተሟላ  ሊሆን  አይችልም።  ኢትዮጵያን  ለማሻገር  የሚደረገው  ጥረትም
                  ፖለቲካውን ከኢኮኖሚው ጋር አስተሳስሮ መመልከት ይጠይቃል።
             ii.   ዛሬ ባለው እጅግ የተሳሰረ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ፣ ያንድን ሃገር የልማት እና
                  ዕድገት  ፈተናዎች  ከዓለም  አቀፋዊው  ሁኔታ  ነጥሎ  ማየት  የማይቻል  ነው።
                  በመሆኑም፣  አብዛኞቹ  በማደግ  ላይ  ያሉ  ሃገሮች  ዋነኛ  የልማት  እና  ዕድገት
                  ፈተናዎቻቸው  በዓለም  አቀፍ  ደረጃ  ከሚታዩ  አበይት  ፈተናዎች  ጋር  በጥብቅ
                  የተሳሰሩ ናቸው። ስለዚህም፣ በቀዳሚነት አሁን በምንገኝበት ሃያ አንደኛው ክፍለ
                  ዘመን በማንኛውም ሃገር የኢኮኖሚ እድገት እና ልማት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖዎች
                  ሊያሳድሩ  ይችላሉ  ተብለው  የሚገመቱትን  ዓለም  አቀፋዊ  ወሳኝ  ክስተቶች
                  ከሃገራችን ልዩ ሁኔታ ጋር አዛምዶ መመልከት ያስፈልጋል።
             iii.   በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ የሳይንቲስቶች (International Panel on
                  Climate Change) ቡድን ጥናት መሰረት፣ የዓለማችን ሙቀት መጠን እ.አ.አ.
                  በ1900  ከነበረበት  በሁለት  ዲግሪ  ሴንቲግሬድ  ከጨመረ  ተመልሶ  ሊተካ
                  የማይችል  (irreversible)  ከፍተኛ  የተፈጥሮ  አካባቢ  ውድመት  ሊያደርስ
                  እንደሚችል ተረጋግጧል።
             iv.   እስካሁን ድረስ በተፈጠረው የዓለም የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር የተነሳ
                  ሃገራችንን  ጨምሮ  በርካታ  ሃገሮች  ተለዋዋጭ  ለሆነ  የከባቢ  አየር  ሁኔታ
                  መለዋወጥ (climate variability) በመጋለጥ ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም፣ እንደ
                  ኢትዮጵያ  ያሉ  ሃገሮች  የሚያወጧቸው  ብሔራዊም  ሆነ  የዘርፍ  የልማት
                  ፖሊሲዎች ለአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚ (climate resilient) የሆነ እድገት
                  ለማምጣት በሚያስችል መንገድ መቀረጽ እና መተግበራቸው አካታች እና ዘላቂ
                  ልማት ለማረጋገጥ በጣም አስፈላጊ ነው።
              v.   የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ባወጣው የ2020 የሰብዓዊ ልማት
                  ዕድገት ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ ባሁኑ ወቅት አላት ተብሎ ከሚገመተው
                  ታዳሽ  የተፈጥሮ  ሃብት  አቅም  (bio-capacity)  99.7%  በመጠቀም  ላይ
                  ትገኛለች። ይህ የሚያመላክተው የሃገሪቱ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃላይ የመሸከም
                  አቅምን ሙሉ ለሙሉ በመጠቀማችን፣ ተጨማሪ ጫና ለማስተናገድ ያለ ቀሪ
                  አቅም ዜሮ መሆኑን ነው።
   107   108   109   110   111   112   113   114   115   116   117