Page 110 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 110

ደስታ መብራቱ


                  ዓይነታዊ እመርታ (Transformational leapfrogging)፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣
           ያብዛኞቹ  የአፍሪካ  ሃገሮች  ፈተና  ከምዕራባዊው  ዓለም  የሚጫንባቸውን  ማንኛቸውም
           አስተሳሰቦች፣  ልማዶች፣  እና  ቴክኖሎጂዎችን  ያለአንዳች  ሃገራዊ  ምልከታ  እና  ለውጥ
           (adaptation) እንዳሉ መቀበላቸው እና ለመጠቀም መሞከራቸው ነው። እንዲህ አይነቱ
           አካሄድ  ከሚፈጥረው  የአስተሳሰብ  ጥገኝነት  ባሻገር  ሃገሮቹን  ጊዜው  ያለፈባቸው
           ቴክኖሎጂዎች ማራገፊያ በማድረግ ከፍተኛ ሃገራዊ ጉዳት ያስከትላል። ለምሳሌም ያህል፣
           እንደ  እ.አ.አ  ከ1990ዎቹ  አጋማሽ  ጀምሮ  ውጤታማ  ያልሆነውን  እና  ኋላቀር  ተደርጎ
           የተወሰደውን ቆሻሻን በማቃጠል (incineration) ሃይል የማመንጨት ቴክኖሎጂ በቅርቡ
           ወደሃገራችን በማስገባት እንደ አዲስ እና ንጹህ ቴክኖሎጂ ለማቅረብ የተደረገው ሙከራ
                       38
           ሊጠቀስ ይቻላል ።
                   ከዚህ  በተጨማሪ፣  ከ65000  ሜጋዋት  በላይ  የሆነ  የኤሌክትሪክ  ኃይልን
           ከታዳሽ የኃይል ምንጮች ማመንጨት የምትችል ሃገራችን የኑክሊየር የኃይል ማመንጫ
           መገንባት  የሚያስችል  ስምምነት  መፈራረሟ  መሰማቱ  የሚያስገርም  ብቻ  ሳይሆን
           የሚያስደነግጥም ነው ።  በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን እንዲህ አይነት የተዛቡ
           የቴክኖሎጂ መረጣ እና ሽግግር ውሳኔዎች ከፍተኛ ዋጋ ከማስከፈላቸውም በላይ የሃገሪቱን
           ዘላቂ ልማት እድሎች ሊያጠቡ ይችላሉ። ይህን መሰል አደጋዎች ለመቀነስ እና ለማስወገድ፣
           ወደ  እኛ  የሚጎርፉ  ማንኛውንም  የቴክኖሎጂ  ውጤቶችን  በጭፍን  የአጋጣሚ  እመርታ
           (incidental  leapfrogging) ተቀብሎ  ከማስተናገድ  ይልቅ  በዕውቀት  ላይ  በተመረኮዘ
           የዓይነታዊ እመርታ መርሆዎች መሰረት ማንኛውንም ቴክኖሎጂን ለሃገሪቱ ልዩ ሁኔታ እና
           ዘላቂ ልማት ግቦች በሚስማማ መልኩ በትኖ መፈተሽ (unpack) እና አስማምቶ ስራ ላይ
           ማዋል ያስፈልጋል።
                  የስነ ህዝብ ትሩፋት (demographic dividend)፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ
           በማደግ ላይ የሚገኙ ሃገሮች በከፍተኛ የህዝብ ብዛት እድገት የመፈተናቸውን ያክል፣ ልዩ
           ተጠቃሚነት ሊሰጣቸው የሚችል እድልም አላቸው። የዚህም ዋነኛ ምክንያት፣ ካደጉት
           ሃገሮች በተቃራኒው፣ የህዝባቸው አብዛኛው ክፍል አምራች በሆነው የእድሜ ክልል ውስጥ
           መገኘቱ ነው። ለምሳሌም ያህል፣ በሃገራችን ውስጥ እ.አ.አ በ2018 ከነበረው አጠቃላይ
           የህዝብ ብዛት ውስጥ ወደ 39 ሚሊዮን የሚጠጋው ክ15 እስከ 34 ዓመት የዕድሜ ክልል
           ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ይኸው ቁጥር እ.አ.አ በ2037 ወደ ሃምሳ ሚሊዮን ከፍ ይላል።
                  በተለያዩ ሃገራዊ እና አህጉራዊ የልማት ሰነዶች እንደተጠቀሰው፣ ለዚህ በከፍተኛ
           ቁጥር እያደገ ለሚሄድ የህብረተሰብ ክፍል የሥራ ዕድል መፍጠር የሁሉም የአፍሪካ ሃገሮች
           ዓብይ ፈተና እንደሚሆን ይታመናል። በሌላ በኩል ግን፣ ይህንን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን
           ወጣት  እና  አምራች  የህብረተሰብ  ክፍል  በአግባቡ  በማበልፀግ  ወደ  ምርታማ  የሰው
           ሃይልነት መቀየር ከተቻለ ሃገሪቱን ወደ ከፍተኛ እድገት ለማሸጋገር ታላቅ አጋዥ ኃይል

           38  በዚህ ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት https://teifaiq.com/2020/09/07/repi-waste-to-
           energy-plant-sunk-misguided/ ይግቦኙ።
   105   106   107   108   109   110   111   112   113   114   115