Page 98 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 98

ደስታ መብራቱ


              v.   ከዚህ  በተቃራኒው፣  ተቋማዊ  ተረኮች  አንድን  የተወሰነ  የማህበረሰብ  ክፍል
                  ወይም ቡድን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ዓላማዎች በሚጠቅም
                  መልኩ  የሚቀረጹ  ናቸው።  ተቋማዊ  ተረኮች፣  ከአሳታፊነት  (power  with)
                  ይልቅ  ገዢነት (power over)፣  ከመደጋገፍ ይልቅ መቃቃር፣  ከጋራ እድገት
                  ይልቅ ራስ ወዳድነት (egoism) ጎልቶ የሚታይባቸው ናቸው።
             vi.   እንዲህ  ዐይነት  ተረኮች  በህብረተሰቡ  ውስጥ  የሚኖራቸውን  ተቀባይነት
                  ለማጠናከር ሲሉ፣ ሰፋ ያለ ተቀባይነት ያለውን ማህበረሰባዊ ተረክ በመጥለፍ
                  ለራሳቸው ውሱን ዓላማ በሚጠቅም መልኩ ሲያራምዱት ይስተዋላል።
             vii.   ተረኮች ወደ ግጭት ከሚያመሩበት ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ፣ አንደኛው ወገን
                  በራሱ ተረክ በመታበይ የእኔ የሚለውን ተረክ በሌላው ላይ በኃይል ለመጫን
                  በሚሞክርበት ወቅት ነው። ከ1950ዎቹ ጀምሮ፣ በሃገራችን ለተከሰቱት የፖለቲካ
                  ግጭቶች እና የርስ በርስ ጦርነቶች ዋነኛው መነሻም በእንደዚህ አይነት መታበይ
                  የአንድ ወገን ተረክን በሌላው ላይ ለመጫን ከሚደረግ ጥረት ጋር የተያያዘ ነው።
            viii.   እንዲህ አይነቱን ሁኔታ በሰላማዊ ሂደት መፍታት በማይቻልበት ጊዜ፣ የምህዳሩ
                  በከፍተኛ ቀውስ መናጥ እና ይህንን ተከትሎም ቀውሱን ለመሻገር የሚያስችል
                  የስክነት  እና  አስተውሎት  ተዋናዮች  መኖር  ሌላኛው  አማራጭ  (default
                  option) ይሆናል።
             ix.   በምህዳራዊ  አስተሳሰብ  መሰረት፣  በማናቸውም  ህብረተሰብ  ውስጥ  የሚገኙ
                  ተቃራኒ  ተረኮችን  (conflicting  narratives)  ወደ  ዐይነታዊ  የለውጥ  ተረክ
                  (transformational  narratives)  ማምጣት  ያንን  ማህበረሰብ  በዘላቂነት
                  ወደፊት ለማሻገር ቁልፍ እና አይነተኛ እርምጃ ነው።
              x.   ዓይነታዊ የለውጥ ተረኮችን ለማበልጸግ በስራ ላይ ከሚውሉት መርሆዎች አንዱ
                  እና ዋነኛው፣ በልዩ ልዩ ምክንያት አወዛጋቢ እና አጨቃጫቂ የሆኑ ጉዳዮችን
                  ለቀጣይ  ሂደት  በማቆየት፣  አብዛኛውን  ወገኖች  ሊያግባቡ  በሚችሉ  ዋና  ዋና
                  ሰበዞች ላይ ተመርኩዞ የጋራ ሃገራዊ ራዕይ መስረቶችን ማጠናከር ነው።
             xi.   የብሔራዊ  መግባባት  ውይይትን  ውጤታማ  ለማድረግ  ቁልፉ  መለኪያ
                  አጠቃላይ  ሂደቱ  ትብብራዊ  አስተሳሰብን  (collaborative  thinking)
                  በሚያጠናክር  መልኩ  እንዲዋቀር  ማድረጉ  ላይ  ነው።  ይህም  ሶስት  ምዕራፍ
                  ባለው ሂደት ውስጥ ማለፍን ይጠይቃል።
             xii.   እነኚህም፣ የተለያዩ ሃሳቦችን እና አቋሞችን ምንም ያህል የተቃረኑ (divergent)
                  ቢመስሉም  ከልብ  ለመስማት  እና  ለመደማመጥ  የሚያስችል  ዝግጁነት
                  መፍጠርን፣  ለተቃራኒ  አመለካከቶች  መነሻ  የሆኑ  ተጨባጭ  እና  ግምታዊ
                  ስጋቶችን  ለመረዳት  መጣር  እና  አዲስ  እይታ  እንዲፈልቅ  (emergence)
                  ማድረግ፣ እና በመጨረሻም ለምንፈልገው የፖለቲካ ሥርዓት አስፈላጊ በሆኑ
                  ዋና  ዋና  መዋቅራዊ  መሰረቶች  ላይ  መግባባትን  (convergence)  መፍጠር
                  ይሆናል።
   93   94   95   96   97   98   99   100   101   102   103