Page 95 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 95
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
ይሆናል። የመጨረሻው ደረጃ፣ ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ሂደቶች በተፈጠረው መደማመጥ
እና መተማመን ላይ ተመርኩዞ እንዲኖረን ለምንፈልገው የፖለቲካ ሥርዓት አስፈላጊ በሆኑ
ዋና ዋና መዋቅራዊ መሰረቶች ላይ መግባባትን (convergence) መፍጠር ይሆናል።
እንዲህ ዓይነቱ የትብብራዊ አስተሳሰብ ሂደት፣ ከቤተሰብ እስከ ሃገረ መንግሥት፣
ከአነስተኛ ድርጅት እስከ ዓለም አቀፋዊ ኩባንያ ሊሰራ የሚችል ያስተሳሰብ ሂደት መሆኑ
የተረጋገጠ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቢያዳብረው ይጠቅማል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ከመወያያ ርዕስ መረጣ እስከ ጽሁፍ ዝግጅት፣ አቀራረብ እና
የውይይት አደረጃጀት ድረስ ያሉትን ሂደቶች በጥንቃቄ መንደፍ እና ማዘጋጀትን
ይጠይቃል። የመወያያ ርዕስ መረጣን በሚመለከት ለብሔራዊ መግባባት ውይይት
የሚመረጡ ርዕሶች የዲምክራሲያዊ መፎካከሪያ ምህዳሩን ጤናማነት ለማጠናከር አስፈላጊ
የሆኑ የመተባበሪያ ርዕሶች ሊሆኑ ይገባቸዋል። የዚህ ዋነኛው ምክንያት፣ የመፎካከሪያ
ርዕሶችን ለውይይት መምረጡ ከመግባባት ይልቅ መቋጠሪያ ወደሌለው ንትርክ የሚያስገባ
በመሆኑ ነው። ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ለሁለተኛው ዙር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ
ምክር ቤት ውይይት ከተመረጡት ርዕሶች አንደኛው ከፓርቲዎች መብዛት ጋር በተያያዘ
የፓርቲዎች አደረጃጀትን የሚመለከት ጥናታዊ ጽሁፍ እንዲሆን መወሰኑን በሚድያ ሲነገር
ተሰምቷል። ዛሬ ሃገሪቱ ካሉባት በርካታ የፖለቲካ አጣብቂኞች አኳያ ይህ ርዕስ በምንም
አይነት መመዘኛ ለብሔራዊ መግባባት የሚመጥን ካለመሆኑም በላይ፣ አወዛጋቢ የመሆን
እድሉም ከፍተኛ ይሆናል።
በመሰረቱ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አደረጃጀት እና ብዛት በእንደዚህ አይነት
ስብሰባ ለመወስን መሞከር የኢዴሞክራሲያዊነት ዝንባሌም ያለው ይመስላል። ይህንን
ሁኔታ ባግባቡ ለማስተናገድ ማንኛውም ፓርቲ እንደፓርቲ ለመመዝገብ እና ከምርጫም
በኋላ በሚያገኘው የህዝብ ድምጽ ላይ ተመርኩዞ ሊኖረው የሚችለውን ፖለቲካዊ መብት
በምርጫ ህጉ ውስጥ በአግባቡ እንዲካተት ማድረግ ተገቢ ነው። ነገር ግን፣ ይህንን ሂደት
አካታች በሆነ ሂደት በባለቤትነት መምራት ያለበት ገለልተኛ እንዲሆን የሚጠበቀው
የምርጫ ቦርድ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አይደለም።
የብሔራዊ መግባባት ውይይት አንደኛው መሰረታዊ ግቡ፣ በፖለቲካ ተዋንያኖች
መካከል ሊኖር የሚገባውን ትብብራዊ አስተሳሰብ ማጠናከር ነው። በዚህ ረገድ፣
ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጽሁፎች የሚዘጋጁበት እና የሚቀርቡበት መንገድ ወደዚህ ግብ
የሚደረገውን ጉዞ ከሚወስኑት አካሄዶች አንዱ እና ዋነኛው ነው። እስካሁን በተካሄዱት
ውይይቶች በተመረጡት ርዕሶች ላይ የመወያያ ጽሁፎች የማቅረቡ ሃላፊነት የተሰጠው
ከፓርቲዎች ውስጥ ለተመረጡ ግለሰቦች በተናጠል ነው። እንዲህ አይነቱ አካሄድ፣
በአቅራቢው በኩል ጽሁፉን ምንም ያህል ሚዛናዊ ለማድረግ ቢሞከር፣ በፓርቲው
መስመር ለመጠለፍ ወይንም በፓርቲ ወገናዊነት ለመኮነን አደጋ መጋለጡ የበዛ ነው።
87