Page 92 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 92

ደስታ መብራቱ


                                                33
           6.3 ለብሔራዊ መግባባት ውይይት ውጤታማነት
                  ላለፉት በርካታ ዓመታት በሃገራችን በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ መመሰቃቀል
           ለመረዳት እና መፍትሄ ለመሻት የብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ሲነሳ እና
           ሲጠየቅ እንደነበር ይታወቃል። ይህንንም እውን ለማድረግ በተለያዩ ዜጎች እና የበጎ ፍቃድ
           ቡድኖች  ልዩ  ልዩ  ጥረት  ሲደረግ  ቆይቷል።  ነገር  ግን፣  ከእነኚህ  ጥረቶች  አብዛኞቹ  ወይ
           በጅምር  ከሽፈዋል  አለበለዚያም  በውሱን  ውጤታማነት  ተጠናቀዋል።  ለዚህም  በርካታ
           ምክንያቶች  ሊጠቀሱ  የሚችሉ  ቢሆንም  የሂደቶቹ  አካታች  አለመሆን  እና  በስልጣን  ላይ
           ያለው ፓርቲ ለሂደቶቹ የነበረው ፈቃደኝነት ውሱን መሆን በዋነኝነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
           በቅርቡ  በሠላም  ሚኒስቴር  እና  በኢትዮጵያ  የፖለቲካ  ፓርቲዎች  የጋራ  ምክር  ቤት
           አማካኝነት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ለማካሄድ
           የተደረሰው  ስምምነት  እና  ይህንንም  ተግባራዊ  ለማድረግ  በፖለቲካ  ፓርቲዎች  መሃል
           እየተካሄደ የሚገኘው ውይይት ከላይ የተጠቀሱትን መሰረታዊ ችግሮች በማስወገድ ረገድ
           የተሻለ እድል ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል። በመሆኑም፣ ሁሉም የዚህች ሃገር የወደፊት እጣ
           ፈንታ  የሚያስጨንቀው  ወገን  ሊያበረታታው  እና  ህዝባዊ  እና  ሙያዊ  ድጋፍ  ሊቸረው
           ይገባል። ይህንን ለሃገሪቱ መጻኢ ዕድል ወሳኝ የሆነ ሂደት የሚመሩ እና የሚያስተባብሩ
           ወገኖችም  ሂደቱ  ውጤታማ  እንዲሆን፣  ካለፉ  መሰል  ጥረቶች  መማር  እና  ለችግሩ
           ውስብስብነት  በሚመጥን  የአተናተን  ዘዴ  (methodology)  ሂደቱን  መምራት
           ይጠበቅባቸዋል።
                  ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተደረጉ መሰል ጥረቶች መካከል በምሳሌነት ሊጠቀስ
           የሚችለው  የምንፈልጋት  ኢትዮጵያ  (Destiny  Ethiopia)  በሚል  ስያሜ  እየተነቃነቀ
           የሚገኘው ሃገር በቀል ተነሳሽነት ነው። ይህ ሂደት በተከተለው ልዩ ስልታዊ አካሄድ የተነሳ፣
           ምናልባትም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተሻለ ውጤታማነት የታየበት ሂደት ነበር
           ማለት ይቻላል። የዚህ ሂደት የመጀመሪያው ግብ፣ በፖለቲካ ልሂቃኖቹ መሃከል ለዘመናት
           ተኮትኩቶ የተገነባውን አእምሮአዊ አጥር (Mental barriers) ማፈራረስ ነበር። ይህንን
           ግብ፣ በግለሰብ፣ በቡድን እና በስብስብ ደረጃ በተካሄዱ በርካታ ውይይቶች እና የተግባር
           ልምምዶች  አማካኝነት  በአብዛኛው  ለማሳካት  እንደቻለ  መመስከር  ይቻላል።  ከዚህ
           በመቀጠል  የነበረው  ግብ  የሀገሪቱን  መሰረታዊ  የፖለቲካ  ችግሮች  ሊፈታ  የሚያስችል
           አሻጋሪ ቢሆንሶችን (transformational scenarios) መለየት ነበር።  ይህንንም ለማድረግ
           ከተናጠል  ሁነቶች  እና  ሂደቶች  አሻግሮ  በመመልከት  መዋቅራዊ  ምክንያቶችን  እና
           አእምሮአዊ ምስሎችን (models) መፈተሽ አስፈላጊ ነበር።






           33  የዚህ ክፍል አብዛኛው፣ መስከረም 30 ቀን 2013 በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ታትሟል።
   87   88   89   90   91   92   93   94   95   96   97