Page 89 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 89

ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ


                     ባላፉት  ጥቂት  ዓመታት  ከሚያወዛግቡ  አንዳንዴም  የግጭቶች  መነሻ  ከሆኑ
             ጉዳዮች  አንዱ  የሰንደቅ  ዓላማ  ጉዳይ  ነው።  ይህ  ችግር  ኢህአዴግ  ሁሉንም  ጉዳይ
             የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቅኝት ለመስጠት ካለው አምባገነናዊ አባዜ ጋር ተያይዞ በሀገራዊ
             ሰንደቅ ዓላማ እና መንግስታዊ አርማ መካከል ከፈጠረው መደበላለቅ ጋር የተያያዘ ነው።
             የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን ብንመለከት፣ በንጉሡ ዘመን የሞዓ እንበሳ አርማ ያለበት ሰንደቅ
             ዓላማ ንጉሱ በሚኖሩበት እና በሚገኙበት ስፍራ ብቻ የሚውለበለብ ሲሆን በደርግ ጊዜም
             የወታደራዊው ደርግ ዓርማ ያለበት ባንዲራ በቤተ መንግስት እና በዋና ዋና መንግስታዊ
             መስሪያ  ቤቶች  ሲውለበለብ  ኖሯል።  ከዚህ  ውጭ፣  አጠቃላዩ  የኢትዮጵያ  ህዝብ
             የሚያውቀውም ሆነ በየቤቱ ደጃፍ የሚያውለበልበው ሰንደቅ ዐላማ ለዘመናት የዘለቀው
             ባለ ሶስት ቀለሙን ሰንደቅ ዓላማ ነው።
                     በመሰረቱ፣ ማንኛውም ዜጋ እንኳንስ ሃገራዊ ሰንደቅ ዓላማን አይደለም፣ ሃሳቡን
             እና እምነቱን ይወክላል የሚለውን ማንኛውንም አርማ ይዞ መዘዋወር ሃሳቡን በነጻነት
             የመግለጽ  ህገ  መንግስታዊ  መብቱ  አካል  ተደርጎ  ሊወሰድ  ይገባል።  በዚሁ  አገባብ፣
             መንግስታዊ  ተቋማት  መንግስታዊ  አርማ  ያለበትን  ሰንደቅ  ዓላማ  ማውለብለብ
             የሚጠበቅባቸው  ሲሆን  ሌሎች  ዜጎች  ግን  እንደምርጫቸው  ባለዓርማውንም  ሆነ
             መደበኛውን ሰንደቅ ዓላማ የመያዝ እና የመጠቀም ነጻነታቸው ሊጠበቅ ይገባል። ይህንን
             በማድረግም፣  በሰንደቅ  ዓላማ  ዙሪያ  ሊኖር  የሚገባውን  ሃገራዊ  አንድነት  ማጠናከር
             ይቻላል።

                      በቅርቡ የተከሰተው ሃገራዊ ቀውስ አንድ አቢይ ጠቃሚ ጎኑ በከፍተኛ ደረጃ
             የፈጠረው ሃገራዊ የአንድነት ስሜት ነው። ይህ ደግሞ፣ አከራካሪ በሆኑ አበይት የፖለቲካ
             ጉዳዮች ላይ ወደ ዓይነታዊ የለውጥ ተረኮች ሊወስዱ የሚያስችሉ መግባባቶችን ለማዳበር
             የሚያስችል ሁኔታ ፈጥሯል። ከነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው በስራ ላይ ያለው
             ህገ መንግስት መነካት የለበትም በሚሉ እና ህገ መንግስቱ ሙሉ በሙሉ መቀየር አለበት
             በሚሉ  ሁለት  ተቃራኒ  ተረኮች  ዙሪያ  ይሽከረከራል።  ከዓይነታዊ  የለውጥ  ተረክ  አኳያ
             ለሃገሪቱ ሽግግር እጅግ ጠቃሚ የሚሆነው በእነዚህ ጽንፍ አቋሞች ዙሪያ መነታረክ ሳይሆን
             በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ውስጥ ያሉትን መሰረታዊ የተቃርኖ ምንጮች ማድረቅ ነው።
                     ከዚህ  ውስጥ  ዋነኛው  በስራ  ላይ  ያለው  ህገ  መንግስት  ‘የሀገሪቱ  ሉዓላዊነት
             ባለቤት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ናቸው’ ብሎ ይደነግጋል። ነገር
             ግን፣  በዚሁ  ህገ  መንግስት  መሰረት  የተቋቋሙት  አብዛኞቹ  የክልል  መንግስታት  ህገ
             መንግስቶች ‘ህዝቦች’ የሚለውን ቁልፍ ህገ መንግስታዊ ቃል እንደሌለ በመቁጠር ክልሎችን
             የአንድ ወይንም የተወሰኑ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ብቻ እንደሆኑ አድርገው ደንግገዋል።
             እንዲህ ዓይነቱ ኢህገመንግስታዊ አካሄድም ለበርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ ህይወት
             መጥፋት እና ህዝቦች መፈናቀል ዋነኛ መነሻ ሆኗል።




                                                                        81
   84   85   86   87   88   89   90   91   92   93   94