Page 90 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 90
ደስታ መብራቱ
ወደፊት ሊያራምደን የሚችለው ዓይነታዊ የለውጥ ተረክ በስራ ላይ ባለ ህገ
መንግስታዊ ሥርዓት ውስጥ ያሉትን ጎጂ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ይዘቶች እና ተቃርኖዎች
በሂደት በመንቀስ ለሁሉም ህዝቦች መሰረታዊ መብት መከበር መስራት ነው። ለዚህም
አብዩ የአጭር ጊዜ መፈተሻ፣ በመጪው ሃገራዊ ምርጫ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ
በየትኛውም የሚኖርበት ክልል በነጻነት መምረጥ እና መመረጥ የሚችልበትን ሁኔታ
ማስከበር እና በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ህዝቦች በነጻነት በመረጧቸው
መሪዎቻቸው የመተዳደር መብታቸውን ማክበር ይሆናል።
ከህገ መንግስቱ ጋር የተያያዘ ሌላው አከራካሪ ጉዳይ የፌዴራል አወቃቀር
ሥርዓቱ ነው። አንደኛው ተረክ፣ ‘ዛሬ ያለው የክልል አወቃቀር የብሔር ብሔረሰቦችን
ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያስከበረ በመሆኑ ሊነካ አይገባም’ ሲል፣ የዚህ ተቃራኒው
ተረክ ደግሞ ‘አሁን ያለው የክልል አወቃቀር ሃገሪቱን ለማያባራ የህዝቦች ግጭት የዳረገ
በመሆኑ ሊፈርስ እና በሌላ አደረጃጀት ሊተካ ይገባዋል’ ይላል። በዚህ ፀሃፊ ዕምነት፣
የወቅቱ ዋነኛ የፖለቲካ ችግር በስራ ላይ ያለው የክልል አከላለል ሳይሆን የፌዴራል
ሥርዓቱ ዲምክራሲያዊ አለመሆን ነው። ስለዚህም፣ የዓይነታዊ ለውጥ ትርክቱ ትኩረት
መሆን ያለበት እንዴት አሁን ያለውን የፌዴራል አከላለል ዴሞክራሲያዊ እናድርገው
መሆን የኖርበታል።
ለዚህም አብዩ የአጭር ጊዜ መፈተሻ፣ አንደኛ፣ በሃገሪቱ ህገ መንግስት አንቀጽ
ስምንት መሰረት ባሁኑ ሰዓት በሃገሪቱ የሚገኙ ክልሎች ባለቤቶች በየክልሉ ውስጥ
የሚኖሩ ህዝቦች በሙሉ እንጂ የአንድ ወይንም የተወሰኑ ብሔረሰቦች ብቻ አለመሆናቸውን
አምኖ መቀበል፤ ሁለተኛ፣ በክልሎች መካከል የሚገኘው መለያ አስተዳደራዊ ወሰን እንጂ
ሃገራዊ ድንበር አለመሆኑን መረዳት እና እንዳስፈላጊነቱ በግጭት ሳይሆን በህዝቦች ቀጥተኛ
ተሳትፎ እና ውሳኔ ሊቀየሩ የሚችሉ መሆናቸውን መቀበል፤ እና ሶሰተኛ፣ የፌዴራላዊው
አስተዳደር መሰረት የሆኑት የወረዳ አስተዳደሮች የህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር
ተግባራዊነት ዋነኛ መገለጫዎች መሆናቸውን አምኖ በክልሎች የተማከለውን አስተዳደር
ወደ ህዝቡ ማቅረብ ይሆናል። ይህንን በማድረግም፣ አሁን ያለውን የፌዴራል ሥርዓትን
ዴሞክራሲያዊነት በተግባር ማጠናከር ይቻላል።
በመጨረሻም፣ ከዚህ በላይ ከተመለከትናቸው የህገ መንግስት እና ፌዴራል
አወቃቀር ጋር የተያያዘ ሌላው አከራካሪ ጉዳይ የቋንቋ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ፣ ከህዝቦች
ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መከበር አኳያ፣ እያንዳንዱ ክልል በክልሉ ውስጥ
የሚገኘው አብዛኛው ህዝብ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሆነውን የክልሉ ዋነኛ የስራ ቋንቋ ማድረጉ
ያለው ጠቀሜታ የሚያከራክር አይሆንም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በህዝቦች አንድነት ላይ
የተመረኮዘ ፌዴራላዊ ሥርዓት እንዲኖረን ከተፈለገ ለሃገራዊ መግባባት የሚያገለግል ቋንቋ
መኖር አስፈላጊነትን መገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ፣ በህገ መንግስቱ የፌዴራል
መንግስቱ የስራ ቋንቋ የሆነው በክልሎች አስተዳደር መስሪያ ቤቶች እንደ ሁለተኛ ቋንቋ
አለመስራቱ ሥርዓቱን ከፌዴራላዊ ይልቅ የኮንፌዴራላዊ ሥርዓት አስመስሎታል።