Page 88 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 88

ደስታ መብራቱ


           ካቀረቡት  ማብራሪያ  ውስጥ  አንደኛው  ነጥብ  የሃገር  መከላከያ  ሰራዊት  የብሔራዊ
           አንድነታችን እና ሉዓላዊነታችን መገለጫ መሆኑን በማስመር ይህንን የሃገር አንድነት ኃይል
           ከማናቸውም የፖለቲካ ቡድን ተጽእኖ ነጻ ማድረግ እንደሚገባ ነው።

                  በዚህ ረገድ፣ በህብረተስቡ ውስጥ ሊሰራ ከሚገባው የማስተማር እና ማሳወቅ
           ተግባር ባሻገር፣ መንግስት እና የፖለቲካ ቡድኖችም ከእንግዲህ ወዲያ የሃገር መከላከያ
           ሠራዊትን በምንም አይነት ሁኔታ ለፖለቲካ ዓላማቸው መጠቀሚያ ከማድረግ መቆጠብን
           እንደ መሰረታዊ አገራዊ መርህ መቀበል እና ማክበር ይኖርባቸዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣
           በክልል  መስተዳድሮች  የሚደራጁት  ልዩ  ኃይሎች  የሃገርን  ልዕልና  በማፍረስም  ይሁን
           በማስከበር  ሊኖራቸው  የሚችለውን  ድርሻ  በሰሜኑ  የሃገራችን  ክፍል  የተፈጠረው
           ወታደራዊ  ቀውስ  በግልጽ  አሳይቶናል።  እንዲህ  ዓይነት  ኃይሎች  በሃገር  ህልውና  ላይ
           ሊያስከትሉ  የሚችሉትን  ጥፋት  ለመቀነስ  የክልል  ልዩ  ኃይሎች  አደረጃጀትን  ከህገ
           መንግሥታዊ ሥርዓቱ አኳያ መመርመር እና ማስተካከል ያስፈልጋል።
                  ሌላው  በጠቅላይ  ሚኒስትሩ  ማብራሪያ  ላይ  የተጠቀሰው  አቢይ  ነጥብ፣
           የተመዘገበውን ወታደራዊ ድል በተመለከተ የትኛውም ወገን በድል አድራጊነት ስሜት ወደ
           መታበይ እንዳይሄድ የሰጡት ማሳሰቢያ ነው። ይህ አባባል እንደ ማንኛውም አባባል በግርጌ
           ማስታወሻነት (footnote) የሚታለፍ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ
           ፋይዳ ያለው ቁምነገር ነው። የወቅቱን የመንግስት ስልጣን ጠቅልሎ በያዘ ድርጅት መሪም
           መነገሩ ታላቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ይህንን ለመረዳት፣ ሩቅ ሳንሄድ የደርግ መንግስት
           የሶማሊያውን ድል ከተቀዳጀ በኃላ እና የኢህአዴግ መንግስት ከኤርትራው ድል በኃላ
           በምን ያህል ፍጥነት ወደ ለየለት አምባገነናዊነት እንደተቀየሩ ማስታወሱ በቂ ይሆናል።

                  በህወሃት  ላይ  የተገኘውን  ድል  ተከትሎም፣  እንዲህ  አይነቱ  አዝማሚያ
           በአንዳንድ ፖለቲካ ሹመኞች አካባቢ መታየት ጀምሯል። በሚያስገርም ሁኔታ፣ እነኚህ
           አዝማሚያዎች  በስልጣን  ላይ  ካለው  ፓርቲ  በበለጠ  ተቃዋሚ  ተረክ  በሚያራምዱ
           ፖለቲካኞች እና ተንታኞች አካባቢ ጎልቶ ታይቷል። ይህም፣ በጦርነቱ የተገኘውን ድል
           በማስታከክ አስቀድሞም ተናግረን ነበር አሁንም መሆን ያለበት እንደዚህ ነው በማለት
           የአንድን  ወገን  ፖለቲካዊ  ተረኮች  የበላይነት  ለማስረጽ  በሚደረጉ  ጥረቶች  ይገለጻሉ።
           እንዲህ አይነት አመለካከቶች በጦርነቱ የተፈጠረውን የሃገራዊ አንድነት ስሜት የሚሸረሽሩ
           ከመሆናቸውም በላይ ለዓመታት ሲብላሉ በቆዩት ተቃራኒ ተረኮች መካከል ያለውን ግጭት
           እንዲባባስ  ሊያደርገው  ይችላል።  ከዚህ  ይልቅ፣  ከየትኛውም  ወገን  ሊመጣ  የሚችልን
           የመታበይ ስሜት በመቋቋም እና ለሌላ የተወሳሰበ ችግር ሊዳርጉ ከሚችሉ ያንድ ወገን
           ተረኮች በመቆጠብ መጪውን ሃገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ተዓማኒ ማድረጉ ላይ
           ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ ተገቢ ይሆናል።
   83   84   85   86   87   88   89   90   91   92   93