Page 83 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 83
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
እስከዛሬ ለነበሩትና አሁን ላለንበት ውስብስብና አስቸጋሪ ሁኔታ ከፍተኛ
አስተዋጽኦ ካደረጉ አበይት ችግሮች አንደኛው በህገ መንግስታዊ ሥርዓትና በፖለቲካ
ርዕዮተ ዓለም መካከል ያለው የጽንሰ ሃሳብና የተግባር መደበላለቅ ነው። ባለፉት ሁለት
ዓመታት የትግራይ ክልል መስተዳድር በፌዴራል መንግስቱ ላይ ካሰማቸው ክሶች
አስገራሚው የፌዴራል መንግስቱ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ጥሷል የሚለው ውንጀላ
ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚወጡ በርካታ ትንተናዎች አንድ መሰረታዊ ችግር
ይታይባቸዋል። ይህም ህገ መንግስታዊ ሥርዓትን ካንዱ ወይም ከሌላው ዓይነት የፖለቲካ
ርዕዮት ዓለም ጋር አዛምዶ የመመልከት ችግር ነው። ይህ ችግር በዋነኝነት በህወሃት እና
መሰል የፖለቲካ ድርጅቶች አመራር ውስጥ ገኖ የሚታይ ችግር ነው። በመሆኑም፣
ለህወሃት አመራር ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ማለት በአብዮታዊ ዲምክራሲ የፖለቲካ
አስተሳሰብ የተቃኘ መንግስታዊ ሥርዓት ብቻ አድርጎ በመውሰድ፣ ከዚህ የተለየ አካሄድ
መከተል ኢ-ህገ መንግስታዊነት አድርጎ ይደመድማል።
እንዲህ አይነቱ አመለካከት ባንድ ሃገር ውስጥ ያለን የፖለቲካ ምህዳር አረዳድ
የተዛባ ከማድረጉም በላይ የፖለቲካ ድርጅቱ የራሱን ድምጽ የሚያዳምጥበት ሳጥን (echo
chamber) ውስጥ ታጥሮ ከገሃዱ እውነታ ጋር እንዲጣላና ወደ አምባገነናዊነት ወይም
ወደ ውድቀት እንዲያመራ ያደርገዋል። ይህን መሰል ሁኔታ ዛሬ በህወሃት ብቻ የተከሰተ
ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት የፖለቲካ ሥርዓቶች ላይም የታየ እና ወደፊትም በሌሎች
ላይ ሊታይ የሚችል ችግር ነው። ስለዚህም፣ እንዲህ አይነቱን መደበላለቅ የፈጠሩ እና
ወደፊትም ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ከመሰረቱ መረዳትና መፍትሄውንም መሻት አሁን
አጋጥሞን ያለውን አይነት ፈተናዎች ለመቀነስ አይነተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ለዚህም፣
ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች ሊገነዘቡት የሚገባው ቁም ነገር፣ ያንድ ሃገር ህገ መንግሥት
ዴሞክራሲያዊ ሊባል የሚችለው በተለያየ ርዕዮት ዓለም የተቃኙ የፖለቲካ መስመሮች
በህዝብ የመጨረሻ ውሳኔ ሊስተናገዱ የሚችሉበትን ማዕቀፍ ሲፈጥር ብቻ መሆኑን ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአበይትነት ሊነሳ የሚችለው መዋቅራዊ ጥያቄ ባሁኑ ወቅት
በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ጉዳይ ነው። የማናቸውም ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ዋነኛው
መሰረቱ ህገ መንግስቱ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ላይ ልዩ ትኩረት ማድረጉ ተገቢ ነው።
ነገር ግን፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚካሄዱ ትንተናዎች በህገ መንግሥት እና በህገ
መንግሥታዊ ሥርዓት መካክል ያለውን አንድነት እና ልዩነት ሲያደበላልቁት ይስተዋላል።
ከምህዳራዊ ትንተና አኳያ፣ ህገ መንግሥት ያንድ ሃገር የፖለቲካ ሥርዓት የሚመሰረትበት
ዋነኛው የህግ ሰነድ ሲሆን፤ ያንድ ሃገር ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት በህገ መንግሥቱ ላይ
ተመርኩዘው የሚወጡ ዝርዝር ህጎችን እና ህገ መንግሥቱን ለማስፈጸም የሚደራጁ
ተቋማትን ያካትታል።
75