Page 82 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 82

ደስታ መብራቱ


           በኢትዮጵያ ያለውን መሰረታዊ የፖለቲካ ችግር ከስሩ ለመንቀል መልካም አጋጣሚ እንደሆነ
           ሲናገሩ ይደመጣል። በእርግጥም፣ እንዲህ ዓይነት ጦርነቶችና ግጭቶች ወደፊት አላራምድ
           ያሉ  ሁኔታዎችን   በመለወጥ ረገድ  የራሳቸውን  ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ
           ይታመናል።

                  ይህ  ሊሳካ  የሚችለው  ግን፣  ጦርነቱ  የሚፈጥረውን  አጋጣሚ፣  ለምህዳሩ
           ጤናማነት አስቸጋሪ የሆኑ በጥባጮችን (rogue elements) ከማስወገድ ባሻገር ለእንዲህ
           አይነት ሁኔታዎች መፈጠር ምንጭ የሆኑትን መዋቅራዊ ሁኔታዎች መፍታት ሲቻል ነው።
           ይህ ደግሞ፣ ከወታደራዊ ዘመቻው ጎን ለጎን፣ የሰከነ እና የበሰለ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ
           እና  ማህበራዊ  መፍትሄዎችንም  ማፈላለግ  ይጠይቃል።  እንዲህ  አይነት  ሁሉን  አቀፍ
           የመፍትሄ  አቅጣጫን  መከተል  ወታደራዊ  መፍትሄ  የሚጠይቀውን  መስዋእትነት
           ከመቀነሱም በላይ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ችግር የሚፈጠርበትንም ሁኔታ ይቀንሰዋል። ይህ
           ክፍል፣ ይህንን ለማድረግ የሚያስፈልጉንን የአመለካከት ለውጦችና ሊተኮርባቸው የሚገቡ
           አበይት መዋቅራዊ ጉዳዮችን ይጠቁማል።
                  በአሁኑ ወቅት፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ አጋጥሟት የማያውቅ እጅግ ፈታኝ
           የሆነ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል
           እና  በሌሎችም  አካባቢዎች  የሚከፈለው  መስዋእትነት  ትርጉም  የሚኖረው  ለዘመናት
           ተጣብቶን  የኖረውን  የፖለቲካ  ምስቅልቅል  ከምንጩ  ለማድረቅ  ወደሚያስችል  ዕድል
           መቀየር ከቻልን ብቻ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከሁሉ በማስቀደም፣ እንዴት ዛሬ
           ላለንበት አሳዛኝና አሳፋሪ የፖለቲካ ምስቅልቅልና ጦርነት ልንደርስ እንደ በቃን ሁሉም
           የፖለቲካ ተዋንያኖች እና ልሂቃን በሃቀኝነት የነፍሲያ ፍተሻ (soul searching) ሊያደርጉ
           ይገባል። እዚህ ላይ፣ ባሁኑ ሰዓት በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ላለው አሳዛኝ ሁኔታ በዋነኝነት
           የህወሃት  አመራር  ባለፉት  የሽግግር  ዓመታት  ውስጥ  የተከተለው  ግትርና  ለውይይትና
           ሽምግልና ያስቸገረ አካሄድ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ አያጠያይቅም። በመሆኑም፣
           በዚህ  ግጭትና  ጦርነት  ለተፈጠረው  ሰብዓዊና  ቁሳዊ  ውድመት  ቀዳሚ  ተጠያቂነት
           ይኖርበታል።

                  ይህ እንዳለ ሆኖ፣ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ከሚመራው የፖለቲካ ፓርቲ
           ጀምሮ ሁሉም የፖለቲካ ተዋንያን ወይ መደረግ የማይገባውን ወቅት ሳይጠብቁ በማድረግ፣
           አለበለዚያ  ማድረግ  የሚገባቸውን  በወቅቱ  ባለማድረግ  (acts  of  commission  or
           omission)  ለሁኔታዎች  መባባስ  የየራሳቸውን  ድርሻ  እንዳበረከቱ  መረዳት
           ይጠበቅባቸዋል። ይህንን እውነታ አለመቀበልና ችግሩን በሙሉ ‘ከሰይጣናዊው’ የህወሃት
           አመራር ጋር በማያያዝ ሁሉም ፈተና ይህንን ድርጅት በማስወገድ ሊጠፋ እንደሚችል
           አድርጎ ማሰብ ሃገሪቱን ለሌላ ተመሳሳይ ችግርና ጥፋት ለማጋለጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
           ይህ እንዳይሆን፣ ሰፊውን የትግራይ ማህበረሰብና አጠቃላዩን የኢትዮጵያ ህዝብ ባሳተፈ
           መልኩ  ለመሰል  ችግሮች  መነሻ  ሊሆኑ  የሚችሉ  ማህበራዊና  ፖለቲካዊ  ችግሮችን
           መመርመርና መፍትሄ መሻት ይጠቅማል።
   77   78   79   80   81   82   83   84   85   86   87