Page 80 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 80

ደስታ መብራቱ


                     29
           6. ተረኮች  እና ብሔራዊ መግባባት
                  በማናቸውም ማህበረሰብ ወይም ሃገር ውስጥ የተለያዩ ማህበራዊ ተረኮች መኖር
           የሚጠበቅ ሲሆን እነኚህ ተረኮች ግን ለግጭቶች መነሻ የሚሆኑት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ
           በማደግ ላይ ባሉ ሃገሮች ውስጥ ብቻ ነው። የዚህም ዋነኛው ምክንያት፣ በተለያዩ ተረኮች
           መካከል የሚኖሩ አለመጣጣሞችን ሲቻል ለማስታረቅ ያም ካልተቻለ ደግም ለመዳኘት
           የሚያስችሉ  ተቋማዊ  አደረጃጀቶች  እና  ሥርዓቶች  ደካማ  መሆናቸው  ነው።  በእንዲህ
           ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሃገሮች ለወደፊት እጣ ፈንታቸው ወሳኝ ከሆነ የሽግግር ወቅት
           ጋር በሚፋጠጡበት ጊዜ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ማካሄድን እንደ አንድ ዓብይ
           መፍትሔ ይጠቀሙበታል። ባለፉት ሰላሳ ዓመታትም፣ የብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት
           በበርካታ የፖለቲካ መሪዎች እና ልሂቃን በተደጋጋሚ መነሳቱም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።
           የብሔራዊ  መግባባት  ውይይት  ዋነኛ  ግቡ  በተለያዩ  ተረኮች  (narratives) መሃል  ያሉ
           ከአነስተኛ ልዩነቶች እስከ ከፍተኛ ተቃርኖዎች የሚደርሱ የግጭት ምንጮችን ማቀራረብ
           እና ማቻቻል ነው። ይህንንም በአግባቡ ለማከናወን፣ የተረኮችን መሰረታዊ ባህርይ መረዳት
           እና ምህዳራዊ መፍትሔዎቻቸውን መሻት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የመጀመሪያው ዓብይ
           ነጥብ፣  ጥልቅ  መሰረት  ባላቸው  ማህበረሰባዊ  ተረኮች  እና  በተቋማዊ  ተረኮች  መካከል
           ያለውን አይነታዊ ልዩነት መረዳት ነው።
                  ማህበረሰባዊ  ተረክ  (social  narrative)፣  አንድ  ማህበረሰብ  የመጣበትን፣
           ያለበትን እና የሚሄድበትን ማህበራዊ ፍኖት የሚረዳበት እና የሚገልጽበት (collective
           sensemaking) ሲሆን የዚያን ማህበረሰብ አባላት አመለካከት  በመወሰን ረገድ ታላቅ
           አቅም አለው። ማንኛውም ማህበረሰባዊ ተረክ የዚያ ማህበረሰብ የእምነት ስርዓቶች እና
           ዕሴቶች (value systems) ምናባዊ ማከማቻም ናቸው። ስለሆነም አንድን ማህበረሰባዊ
           ተረክ ባግባቡ ለመረዳት የዚያን ማህበረሰብ የዕሴት መስረቶችን በጥልቅ መመርመር እና
           መረዳት ያስፈልጋል። ይህን በሚያደርጉበት ጊዜም፣ ማንኛውም ማህበረሳባዊ ተረክ በጊዜ
           ሂደት በሚከሰት ዝግመታዊ ለውጥ ሊቀረጽም ሆነ ሊለወጥ ይችላል ብሎ ከማሰብ ውጭ
           የተሳሳተ የሚባል ማህበራዊ ተረክ እንደማይኖር በመገንዘብ መሆን አለበት። በዚህ መሰረት
           በሃገራችን በኢትዮጵያ ያሉትን ማህበረሳባዊ ተረኮች ብንመረምር፣ ሁሉም ማህበረሰባዊ
           ተረኮች በጋራነት የሚጋሯቸው በርካታ ማህበረሰባዊ ዕሴቶች እናገኛለን። ከእነዚህም አንዱ
           እና ዋነኛው፣ አንዱ ለብዙው፣ ብዙው ለአንዱ የሚተሳሰብበት (collective solidarity)
           ዕሴት ነው።  እነኚህ በዘመናት የመተሳሰር እና የመወራረስ ሂደቶች ውስጥ የዳበሩ የጋራ
           ማህበራዊ ዕሴቶች የማንኛውም ብሔራዊ መግባባት ውይይቶች ዋነኛ መሰረቶች ናቸው።




           29  በትርክቶች (anecdotes)፣ ተረክ (narratives) እና ታሪክ (history) መካከል ያለው
           መደበላለቅ ሌላው ሊጠራ የሚገባው አመለካከት ነው።
   75   76   77   78   79   80   81   82   83   84   85