Page 76 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 76
ደስታ መብራቱ
ኢህአዴግ (ኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር) ባደረሰው የፖለቲካ እና
አስተዳደር በደል የተጎዱ እና የቆሰሉ ወገኖች ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን፣ ዴሞክራሲያዊ
ባህልን ከመገንባት አኳያ፣ የእንዲህ አይነት ወገኖች ትኩረት እና ጥረት መሆን ያለበት የተሻሉ
አማራጮችን በማቅረብ የመሰል ድርጅቶችን እጣ ፈንታ በህዝብ ድምጽ እንዲወሰን ማድረግ
ነው መሆን የነበረበት። ከዚህ በተቃራኒው፣ ማንኛውንም የፖለቲካ ድርጅት በማናቸውም
መንገድ መወገድ እና መጥፋት አለበት ብሎ መናገር የዲምክራሲያዊነት ዋነኛ መሰረት
የሆነውን የህዝብን የመጨረሻ ወሳኝነት መብት መንጠቅ ይሆናል። ስለሆነም፣ በወቅቱ
በህጋዊነት ተመዝግቦ የነበረን የፖለቲካ ድርጅት ለውይይት መጋበዝ የፖለቲካ ችግሮችን
በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባህልን ለማዳበር የሚደረግ ጥረት አካል ተደርጎ መወሰድ
ነበረበት።
በሶስተኛ ደረጃ የሚነሳው፣ ወ/ሮ ሙፈሪያት በሃገሪቱ ውስጥ ህግ እና ሰላምን
ለማስከበር ከፍተኛ ሃላፊነት የተሰጣቸውን ዋና ዋና መስሪያ ቤቶችን የሚመራውን
የሚኒስቴር መስሪያ ቤት በበላይነት የሚመሩ በመሆናቸው ባለፉት ሁለት የለውጥ ዓመታት
በሃገሪቱ ለደረሰው የጸጥታ መናጋት እና ህዝቦች መፈናቀል ዋነኛ ተጠያቂ መሆናቸውን
ይገልጻሉ። በወቅቱ የሰጡትን መግለጫም የማይመለከታቸውን የድርድር ጉዳይ በማንሳት
ድክመታቸውን ለመሸፈን የተደረገ ጥረት እንደሆነ ያመለክታሉ። እንዲህ አይነቱ፣ ሃገሪቱ
ያለባትን የሰላም እና ጸጥታ ችግር ከአንድ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ወይንም ከተወሰነ
የፖለቲካ ቡድን ጋር የማያያዝ ዝንባሌ የፖለቲካ ችግሩን ውስብስብነት አለመረዳት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ፣ የሰላም ሚኒስትርን መሠረታዊ አላማ እና ተግባራት
ካለመረዳት እና የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወገኖች ተነሳሽነት ለተካሄዱ
ውይይቶች እና ድርድሮች ይሰጥ የነበረውን ድጋፍ ካለመገንዘብ የመነጨ ሊሆን ይችላል።
የአንድ የሽግግር ወቅት መንግስት ውጤታማነት የሚወሰነው በእጁ ውስጥ ያለውን የኃይል
እና የማሳመን አቅም (hard and soft power) በሚዛናዊነት ለመጠቀም ባለው ብቃት
ነው። እንዲህ አይነቱ ተግባርም ባንድ የሚኒስትር መስሪያ ቤት የሚከናወን ሳይሆን
አጠቃላዩ የመንግስት መዋቅር የሚረባረብበት ተግባር ነው። በዚህ ረገድ፣ ከቅርብ ጊዜ
ወዲህ ተጠናክሮ የተጀመረውን ህግን የማስከበር ተግባር ከውጤታማ የብሔራዊ መግባባት
ውይይት ጋር ማቀናጀት እጅግ አስፈላጊ ነው። በወቅቱ፣ ወ/ሮ ሙፈሪያት የተናገሩት ነገርም
ይህንን ሚዛን ለመጠበቅ የተደረገ መልካም ጥረት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።
በአራተኛ ደረጃ፣ አንዳንድ ወገኖች ሚኒስትሯ የተናገሩትን ሃሳብ ለህወሃት
ነበራቸው ከሚባለው ስስ ስሜት (sympathy) ጋር በማያያዝ እየተካሄደ ላለው ለውጥ
ያላቸውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት ሞክረዋል። ጥቂቶችም፣ ካሉበት ኃላፊነት
መነሳት አለባቸው ብለዋል። ይህ አሳዛኝ አመለካከት፣ ለረጂም ዘመን ተጠናውቶን የቆየው
ሃሳብን በሃሳብ ከመሞገት ይልቅ ወደ ስም ማጥፋት እና ማጠልሸት (character
assassination) የመሄድ አሳፋሪ የፖለቲካ ቅሪትን ያመላክታል። እንዲህ አይነቱን
አዝማሚያ ሁሉም በሃገራችን ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን የሚሹ ወገኖች