Page 72 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 72
ደስታ መብራቱ
የበለጠ መሆኑ ነው። ሌላው፣ ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረገው ትግል ውስጥ ካላቸው ቁልፍ
ድርሻ ጋር በተያያዘ ፈታኝ ሁኔታዎችን ለመሻገር ያላቸው የስሜት (survival instinct)
ዝግጁነት ነው። ይህም ባብዛኛው፣ የራሳቸውን መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ፍላጎት በመጫን
እና አሳልፎ በመስጠትም ጭምር የሚገለጽ ይሆናል።
ሶስተኛው፣ ተፈጥሮአዊው ዑደትን ለማስቀጠል ካላቸው ልዩ ኃላፊነት እና ድርሻ
ጋር በተያያዘ ከተፈጥሮአዊው ምህዳር ጋር ያላቸው ቅርበት እና ተዛማጅነት (ecological
sensibility) ነው። አራተኛው እና ምናልባትም በሰፊው ካለብን የፖለቲካ ህመም
ለመፈወስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊኖረው የሚችለው ባህሪ፣ ኃይልን መሰረት ካዳረገ (hard
power) አመራር እና የግጭት አፈታት ይልቅ ስሜትን በማለስለስ እና በማሳመን (soft
power) ላይ ለተመረኮዘ መፍትሄ ያላቸው ብልህነት ነው። እነኚህ እና እነኚህን የመሳሰሉ
በርካታ የሴታዊነት ባህርያት እስከዛሬ ድረስ በነበሩ መንግስታዊ ሥርዓቶች ውስጥ
በአግባቡ ባለመካተታቸው የተነሳ የሰው ልጆች ተነግረው ለማያልቁ ጥፋቶች እና እልቂቶች
ሊዳረጉ በቅተዋል። ይህንን ሁኔታ መቀየር፣ ባሁኑ ሰዓት ዓለማችንም ሆነ ሃገራችን
ተጋፍጠውት ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ አካባቢያዊ፣ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎች
ለማለፍ አቢይ ድርሻ እንደሚኖረው ይታመናል።
ወደ ኢትዮጵያ ሁኔታም ስንመጣ፣ ያሉብንን ዙሪያ መለስ ፈተናዎች ባግባቡ
ለመወጣት የሴታዊነት ግብአትን በሁሉም መስኮች እያጠናከርን መሄድ ይኖርብናል።
ይህንን በምናደርግበት ጊዜም፣ ጥረቶቻችንን የይምሰል ሊያስመስሉ ከሚችሉ እና
ውጤታማነታቸውን ከሚያሳንሱ (sub-optimal) አስተሳሰቦች ራሳችንን ማጽዳት
ይጠበቅብናል። ከዚህ ውስጥ የመጀመሪያው፣ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማጠናከር
የምንወስዳቸው እርምጃዎች የየትኛውንም ውጫዊ አካል ቅቡልነት ለማግኘት ብለን
ሳይሆን መሰረታዊ ከሆነው የሴታዊነት ባህርያት ልናገኛቸው የሚገቡንን ማህበራዊ እና
ተፈጥሮአዊ እሴቶች ባግባቡ ለመጠቀም በማሰብ መሆኑን ማመን ነው። በዚህ ላይ
በመመስረት፣ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የማጠናከሩ ተግባር
የቁጥርን ኮታ ለማሟላት ከሚደረግ ጥረት ባሻገር አመራሩ እና አደረጃጀቱ ከሴታዊነት
ባህርያት የሚመነጩትን ጠቃሚ እሴቶች እንደ ግብዓት ለመጠቀም የሚያስችል መሆን
ይኖርበታል።
ከሁሉም በላይ ግን፣ በማንኛውም መንገድ የአመራር ቦታ የሚይዙ እህቶቻችን
ወንዳዊ ሃይለኝነትን (machismo) እንዲላበሱ የሚያስገድዱ ሁኔታዎችን መከላከል እና
በሴታዊነት ልዩ ባህሪያቸው ላይ በመመርኮዝ ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋጽኦ ላይ
ማተኮር ይኖርባቸዋል። ይህ ፈተና፣ በወንዳዊ አስተሳሰብ ከተቃኘው ተቋማዊ ባህላችን
አኳያ ሲታይ በእጅጉ ፈታኝ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ እንደምሳሌ ሊወሰዱ የሚችሉ