Page 70 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 70
ደስታ መብራቱ
ተደጋግሞ እንደሚነገረው፣ የማንኛቸውም ማህበረሰብ አወቃቀር መሰረቱ
ቤተሰብ ነው። ስለሆነም፣ ከሴታዊነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ባግባቡ ለመረዳት የቤተሰብ
አመሰራረት ያለፈበትን ሂደት በጥቅሉ መመልከት ይጠቅማል። የቅድመ ታሪክ ቤተሰብ
አመሰራረት በአብዛኛው ሴቶችን ማዕከል ባደረገ የእማዊነት (matriarchal) ሥርዓት ላይ
የተመረኮዘ እንደነበር ይጠቀሳል። ይህ ሁኔታ በሂደት እየተቀየረ መጥቶ ቀስ በቀስ ወንዶች
ይበልጥ ወሳኝ ወደሆኑበት አባዊ (patriarchal) የቤተሰብ ሥርዓት ተሸጋግሯል። በዚህ
ሽግግር ምክንያት የተፈጠረው የወንዶች የበላይነት በተለያዩ የኢኮኖሚ ሥርዓት እያደገ
ከመጣው የግል ሃብት ክምችት ጋር ይበልጥ እየተጠናከረ ሊመጣ እንደቻለ ይታወቃል።
የሰው ልጅ አደረጃጀት ከቤተሰብ ወደ ማህበረሰብ ከዚያም ወደ ሃገር እያደገ ሲመጣ
የወንዶችን የበላይነት የሚያጠናክረው የአባዊነት አመለካከት ይበልጥ ተቋማዊ መሰረት
እየያዘ ሊመጣ ችሏል።
በዚህም የተነሳ፣ በመላው ዓለም ባሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ሴቶች ሊኖራቸው
የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ስፍራ አሳጥቷቸው ቆይቷል። ይህ በመሆኑም፣
በሴቶች ላይ ከደረሱ በርካታ የመብት ጥሰቶች ባሻገር ባጠቃላይ የሰው ልጆች ከሴቶች
ቀጥተኛ ተሳታፊነት ሊያገኙ የሚችሉትን ጠቀሜታዎች እንዲያጡ አድርጎታል። ለዚህም
አንዱ ማሳያው ከአባዊነቱ ዘመን እየተጠናከረ መምጣት ጋር ተያይዞ እየተበራከተ የመጣው
ግጭት እና ጦርነት ከዚያም ጋር ተያይዞ የተፈጠሩት በርካታ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ
ቀውሶች ናቸው። ከኢንዱስትሪ አብዮት መምጣት ጋር ተያይዞ ሃገሮች በይበልጥ ወደ ህገ
መንግስታዊ ሥርዓት እየተሸጋገሩ ሲመጡ የሴቶች የመብት ጥያቄዎችም በልዩ ልዩ መልክ
መገለጽ እና መነሳት ጀመሩ።
ዘመናዊውን የተደራጀ የሴቶች የመብት እንቅስቃሴ (Feminist movement)
አነሳስን ስንመለከት አሜሪካዊቷ የሴኔካ ፏፏቴ መግለጫ (Seneca Falls Declaration,
1848) አዘጋጅ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ስታንተን እና ጀርመናዊቷ ሶሻሊስታዊ የሴቶች መብት
አቀንቃኝ ወይዘሮ ክላራ ዜትኪን (1857-1933) በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። በአስራ
ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የተጀመረው የአሜሪካው የሴቶች መብት
እንቅስቃሴ በቀዳሚነት ያተኮረው የሃገሪቱ ሴቶች ተነፍገውት የነበረውን መሰረታዊ
የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ማስከበር ላይ ነበር። ይህ እንቅስቃሴ፣ ከሰባ ዓመታት
ያላቋረጠ ትግል በኋላ የዛሬ መቶ ዓመት አካባቢ የአሜሪካ ሴቶች መሪዎቻቸውን
ለመጀመሪያ ጊዜ ለመምረጥ አስችሏቸዋል።
በአንጻሩ፣ ሶሻሊስታዊው የሴቶች መብት እንቅስቃሴ የአሜሪካውን የሴቶች
መብት እንቅስቃሴ የጥቂት ከበርቴዎች እና ንዑስ ከበርቴዎች ስልጣን የመካፈል ጥረት
አድርጎ በመፈረጅ ትኩረቱን የብዙኃን ሴት ገበሬዎች እና ሰራተኞች መብትን ማስከበር ላይ
ያደርጋል። እዚህ ላይ፣ የ1960ዎቹ ሴት እህቶቻችን በሶሻሊስታዊ ርእዮት ታንጸው በወቅቱ
የሃገራችን ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ያበረከቱት የመሪነት አስተዋጽኦ እና የከፈሉት
መስዋዕትነት ሊዘከር ይገባዋል። ምንም እንኳን ገና በርካታ ተግባራት የሚቀሩ ቢሆንም፣