Page 69 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 69
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
5. ሴታዊነት፣ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ጤናማነት
የዓለማችን የሃገረ መንግስት ምስረታ በአጠቃላይ የወንዶች የበላይነት የሰፈነበት
ነው ማለት ይቻላል። ያም ሆኖ፣ በሃገራችን ኢትዮጵያ የሃገረ መንግስት ታሪክ ውስጥ ታላቅ
ስፍራ የነበራቸው ሴት ነገሥታቶች ነበሩ። የ1966 አብዮትን ተከትሎ በመላ ሃገሪቱ ይሰሙ
ከነበሩ ፖለቲካዊ መፈክሮች አንዱ ‘ያለ ሴቶች ተሳትፎ አብዮቱ ግቡን አይመታም’ የሚለው
ሶሻሊስታዊ መፈክር እንደነበር ይታወቃል። ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለፉት
መቶ ዓመታት ሴቶች ባንድ ማህበረሰብ እድገት ውስጥ ያላቸው ሁለንተናዊ ድርሻ ይበልጥ
እውቅና እያገኘ የመጣ ቢሆንም፣ በተግባራዊነቱ ላይ ግን ገና ብዙ ርቀት መጓዝ
ያስፈልጋል። ለዚህም የመጀመሪያው እርምጃ፣ ሴታዊነት ለማንኛውም ማህበረሰብ ዘላቂ
ልማት ሊያበረክታቸው የሚችላቸውን ልዩ አስተዋጽኦ በበቂ ሁኔታ መረዳት ነው።
25
5.1 ሴታዊነት እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተወደሱበት
አበይት እርምጃዎች አንዱ በርካታ ሴት አመራሮችን በመንግስታቸው ውስጥ ማካተታቸው
እና በዘመናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመርያ የሆኑትን የሃገሪቱ ሴት ርዕሰ
ብሔር እንዲሾሙ ማድረጋቸው ነው። እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ፣ የሃገራችን ሴቶች በሃገሪቱ
የወደፊት እጣ ፈንታ ሊኖራቸው የሚችለውን በጎ አስተዋጽኦ ለማበረታት ጉልህ ድርሻ
እንደሚኖረው ይታመናል። ከዚህ እርምጃ ቀደም ሲል፣ ባላፉት ጥቂት አስርተ ዓመታት
ውስጥ ሴቶችን በሚመለከት በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን የተዛቡ አመለካከቶች በማጋለጥ
እና በመታገል የሴቶችን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ
የሚጥሩ ሃገር በቀል ተቋማት እየበዙ መምጣታቸውም አበረታች የለውጥ ምልክት ነው።
እነኝህ እርምጃዎች፣ በተባባሩት መንግስታት እና በአፍሪካ ሕብረት ከተወሰኑት
የሴቶችን የእኩልነት መብት የማረጋገጥ ውሳኔዎች ጋር የተጣጣሙ ከመሆኑም ባሻገር
ለሃገራዊው ፖለቲካ ጤናማነት ከፍተኛ ድርሻ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ነገር ግን፣ እነኝህ
በፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ የህዝብ ተቋማት የተጀመሩ ቀና እርምጃዎች
ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ ሴታዊነት (Feminism) ባንድ ምህዳር ውስጥ
ያለውን ምሉዕ ድርሻ በመረዳት ላይ የተመረኮዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። በዚህ ክፍል፣
ሴታዊነት ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ እንዴት ሊታይ እንደሚገባው እና በኢትዮጵያ
ሁኔታ ሊኖረን የሚገባውን አጠቃላይ አካሄድ ለማመላከት ይሞከራል።
25 የዚህ ክፍል አብዛኛው፣ ነሐሴ 23 ቀን 2012 በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ታትሟል።
61