Page 64 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 64

ደስታ መብራቱ


                  ይህ  እንዳለ  ሆኖ፣  ሶስተኛው  የዳያስፖራ  የፖለቲካ  ዘመን  በመሰረታዊ
           ባህሪያቸው  የሚለያዩ  ሁለት  አበይት  ክፍሎች  እንዳሉት  መገንዘብ  ያስፈልጋል።
           የመጀመሪያው፣ አብዛኛውን ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊ የሚወክለው እና የሃገሪቱን ሰላም እና
           እድገት በጽኑ የሚመኘው ዝምተኛው ብዙኃን (the silent majority) ሲሆን፣ እነኚህ
           ወገኖች  ለሃገሪቱ  እና  ለህዝቡ  ይጠቅማሉ  ለሚባሉ  ጥሪዎች  ሁሉ  ያለብዙ  ጫጫታ
           ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ እና ዕውቀታቸውን የሚያበረክቱ ናቸው። ከዚህ በተቃራኒው
           የሚገኙት ጥቂት ጯሂዎች (the noisy minorities) ጽንፈኛ በሆነ የፖለቲካ አመለካከት
           እና  ስሜታዊ  በሆኑ  የፖለቲካ  ጥያቄዎች  እያደናገሩ  የራሳቸውን  እና  የቡድናቸውን
           ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አላማዎች ለማሳካት የሚሯሯጡ ናቸው።

                  ምንም  እንኳን፣  በዘመነ  ኢህአዴግ  የነበረው  የዳያስፖራ  ፖለቲካ  ጽንፈኝነት
           የበረታበት ቢሆንም ብዙዎቹ ለኢህአዴግ ከነበራቸው ጥልቅ ተቃውሞ የተነሳ ቀጥተኛ
           ያልሆነ ተደጋጋፊነትም ነበራቸው። ይህም በመሆኑ፣ በ2010 በሃገሪቱ ለተከሰተው ሃገራዊ
           ለውጥ  የየራሳቸውን  አስተዋጽኦ  አድርገዋል።  የ2010  ለውጥንም  ተከትሎ፣  ጥቂት
           የዳያስፖራ ፖለቲካ አቀንቃኞች በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ በቀጥታ ለመሳተፍ የተደረገውን
           ጥሪ በመቀበል ወደ ሃገር ውስጥ ሊገቡ ችለዋል። ይህ እድል የ1966 ህዝባዊ ንቅናቄን
           ተከትሎ ከተከሰቱ የፖለቲካ እድሎች ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን ለተመሳሳይ ውድቀት
           ሊያጋልጡት  የሚያስችሉ  ምልክቶችም  በመታየት  ላይ  ይገኛሉ።  አሁን  የተፈጠረው
           መልካም  የለውጥ  አጋጣሚ  እንደ  ሺህ  ዘጠኝ  መቶ  ስልሳ  ስድስቱ  የለውጥ  አጋጣሚ
           እንዳያመልጠን ከዚህ በታች የተመለከቱትን ከዳያስፖራው ፖለቲካ ጋር የተያያዙ መሰረተ
           ቢስ እምነቶችን (myths) ማከም ይገባል።

                  አንደኛው እና ምናልባትም ዋነኛው፣ ጥቂት የ2010 የዳያስፖራ የፖለቲካ ዘመን
           ጽንፈኛ  መሪዎች  እና  አቀንቃኞች  ለተፈጠረው  የለውጥ  ሂደት  ያበረከቱትን  አስተዋጽኦ
           እጅግ አግዝፈው ማየታቸው ነው። ከዚህም የተነሳ፣ በሃገር ውስጥ የነበረው የብዙሃኑን
           የለውጥ ታጋይ ድርሻ አሳንሶ ከመመልከትም ባሻገር ለውጡ ያለ እነሱ አመራር የትም
           ሊደርስ  አይችልም  ብለው  እስከማመን  ይደርሳሉ።  በምህዳራዊ  አስተሳሰብ  መሰረት፣
           በማንኛውም ምህዳር ውስጥ ሊመጣ የሚችል ለውጥ ዋነኛው መሰረቱ (foundation)
           በዚያው  ምህዳር  ውስጥ  ያለው  ውስጣዊ  መስተጋብር  (internal  dynamics)  ሲሆን
           የውጫዊ ሁኔታዎች ድርሻ የዚህን የለውጥ ፍጥነት ከማፋጠን ወይም ከማዘግየት ያለፈ
           አይሆንም።  በመሆኑም፣  ለ2010  ለውጥ  መምጣት  የዳያስፖራው  የአጋዥነት  ድርሻ
           እንደተጠበቀ  ሆኖ፤  ዋነኛው  ድርሻ  ሊሰጥ  የሚገባው  በቀዳሚነት  በሃገሪቱ  የተለያዩ
           አካባቢዎች  ለነበረው  የህዝቦች  ትግል  እና  የወጣቶች  ንቅናቄ  ሊሆን  ይገባዋል።  ከዚህ
           በተጨማሪ፣ ለለውጡ አንጻራዊ ሰላማዊነት የወሳኝነቱን ሚና (determining factor)
           የሚወስደው  በራሱ  በኢህአዴግ  ውስጥ  የተፈጠረው  የለውጥ  አመራር  እና  ከዚህ  ጋር
           ተያይዞ  የተፈጠረው  የኦሮሞ  እና  የአማራ  ህዝቦች  (ኦሮማራ)  ጥምረት  መሆኑ  ብዙም
           አካራካሪ ሊሆን አይገባም።
   59   60   61   62   63   64   65   66   67   68   69