Page 63 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 63
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
ከፍተኛ ጫና አድርጓል።በመሆኑም፣ ሁለተኛው የዳያስፖራ ትውልድ በ1983 በነበረው
የሽግግር አጋጣሚ ትርጉም ያለው ድርሻ ለማበርከት ሳይችል ቀርቷል።
ሶስተኛው የዳያስፖራ የፖለቲካ ዘመን ከአንደኛው እና ከሁለተኛው የዳያስፖራ
የፖለቲካ ዘመን ከተሸጋገረው በተጨማሪ በዘመነ ኢህአዴግ ከሃገር ተሰዶ የወጣውን እና
በተለያየ ህጋዊ የቪዛ ፕሮግራሞች የሄደውን ኢትዮጵያዊ ያካትታል። ይህ ጊዜ ከ1983 እስከ
2010 የነበረውን የኢህአዴግ ዘመን የሚሸፍን ሲሆን ምናልባትም ቀደም ሲል ታይቶ
በማይታወቅ ሁኔታ ጽንፈኝነት የበረታበት የፖለቲካ አመለካከት ገኖ የወጣበት ዘመን ነው።
ለዚህ ሁኔታ መፈጠር፣ በሁሉም ዘመን ከነበሩት መሰረታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ህመሞች
በተጨማሪ የሚከተሉት ሁኔታዎች አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይገመታል። የመጀመሪያው እና
ምናልባትም ዋነኛው ምክንያት፣ ተረኛ ጨቋኝነት (reverse repression) በሚመስል
መልኩ በኢህአዴግ ተግባራዊ የተደረገው በብሔረሰባዊ አሃዳዊነት (Ethnicised
unitarianism) ላይ የተመረኮዘው ፌደራላዊ ሥርዓት ያስከተለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት
እና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ጥልቅ የተጠቂነት ስሜት ነው።
ሁለተኛው አቢይ ችግር፣ ጭፍን በሆነ የተጠቃሚነት ስሜት ፖለቲካውን
በቀጥታ ራስን እና የራስን ቡድን ለማበልጸጊያ ለመጠቀም የተዘጋጁ ግለሰቦች እና የተደራጁ
ቡድኖች እየበረከቱ መምጣታቸው ነው። የእነኚህ የፖለቲካ ነጋዴዎች (political
entrepreneurs) ህልውና የሀገሪቱ ፖለቲካ የተረጋጋ ካለመሆኑ ጋር የተያያዘ በመሆኑ
ጽንፍ የያዙ የፖለቲካ አመለካከቶችን ማራገብ ዋነኛ መገለጫቸው ሊሆን ችሏል።
ሶስተኛው፣ ባግባቡ ያልተብላላ እና ያልበሰለ መረጃን ለማሰራጨት ማህበራዊ ሚዲያ
የፈጠረው አመቺነት እና ከዚህ ጋር በተያያዘ እየገነገነ የመጣው ዋልታ ረገጥነት ነው። በይነ
23
መረብ (internet) እና ማህበራዊ ሚዲያ ማንኛውንም መረጃ በእኩልነት ለሁሉም
ማዳረስ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ሰው መረጃን የማመንጨት አቅምንም ፈጥሮለታል።
በዚህም የተነሳ፣ ማህበራዊ ሚዲያ አንድን ማህበረሰብ ከፍ ወዳለ እድገት ለማሻገር
የሚያስችል የመሆኑን ያህል ለከፍተኛ ጥፋትም ሊዳርግ ይችላል። በዚህ ረገድ፣ የበይነ
መረብን አመቺ ሁኔታ ለህዝብ እና ለሃገር ጥቅም በሚጠቅም መልኩ የሚጠቀሙ በርካቶች
የመኖራቸውን ያህል ጥቂቶች በህዝቦች መካከል መቃቃር እና ግጭት ለመፍጠር
የሚያደርጉት አሳዛኝ አና አሳፋሪ ጥረት ለሃገሪቱ ፖለቲካ መረጋጋት ከባድ ፈተና እየሆነ
መጥቷል። ይህ ሁኔታ፣ በጋዜጠኝነት፣ ማህበራዊ አንቂነት እና በፖለቲከኛነት መካከል
ባለው የሚና መጠላለፍና የሥነምግባር ጉድለት ይበልጥ እየተወሳሰበ ይገኛል።
23 አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ የብዙዎቹ ገበያ ተኮር ማህበራዊ ሚዲያዎች መሰረታዊ
አደረጃጀት (architecture) ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነትን (egocentrism) የሚያበረታቱ
በመሆናቸው፣ ማህበራዊ ደህንነትን እና ትብብርን አደጋ ላይ የመጣል እድላቸው ከፍተኛ ሊሆን
ይችላል። ይህ ሁኔታ፣ በማደግ ላይ ላሉ ሃገሮች በቻ ሳይሆን በቅርቡ በአሜሪካ እንደታየው፣
ለበለጸጉት ሃገሮችም ፈታኝ በመሆን ላይ ይገኛል።
55