Page 62 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 62
ደስታ መብራቱ
እነኚህ ወገኖች በመሃከላቸው የነበረውን ልዩነት እንደያዙ ወደ ሃገር ውስጥ
በመግባታቸው፣ በሃገር ቤት የነበረው ወጣትም በሁለት ጎራ እንዲሰለፍ አድርጎታል። ይህ
ልዩነት፣ በለውጡ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በተወሰዱ የገጠር መሬትን የህዝብ ያደረገውን
አዋጅ በመሳሰሉ ስር ነቀል እርምጃዎች ምክንያት ይበልጥ እየሰፋ በመሄድ ላንድ ትውልድ
የርስ በርስ መተላለቅ የራሱን አሳዛኝ ድርሻ ሊያበረክት ችሏል። በመሆኑም፣ የመጀመሪያው
ትውልድ ዳያስፖራ የ1966 ንቅናቄ ይዞት ለመጣው ሃገራዊ የሽግግር እድል መምጣትም
ሆነ በአጭር መጨናገፍ የራሱን አስተዋጽ አድርጓል ማለት ይቻላል።
የ1966 የህዝብ ንቅናቄን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው ወታደራዊ መንግስት
ስልጣኑን ለማጠናከር የወሰዳቸው ፖለቲካዊ እርምጃዎች በህዝባዊው ንቅናቄ ግንባር ቀደም
ተሳታፊ የነበረውን የተማረ የሰው ኃይል በእጅጉ ሊያመናምነው ችሏል። ይህንን ተከትሎ፣
እስከ 1983 ድረስ በነበረው ከፍተኛ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ቀውስ የተነሳ በመቶ ሺዎች
የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሃገር ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል። ይህም፣ ቀደም ሲል
በአብዛኛው ለትምህርት በወጣው እና አነስተኛ ቁጥር ባለው ኢትዮጵያዊ የሚታወቀውን
የመጀመሪያውን የዳያስፖራ የፖለቲካ ዘመን ገጽታ ቀይሮታል። ከዚህ ከሁለተኛው
የዳያስፖራ የፖለቲካ ዘመን ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ በሁለተኛ ዜግነታቸው
የሚደርስባቸውን በርካታ ፈተናዎች በመቋቋም ኑሮአቸውን ማሸነፍ ላይ ቢያተኩሩም፣
የተወሰኑት ከኑሮው ትግል በተጨማሪ በሃገሪቱ የወደፊት የፖለቲካ እጣ ፋንታ ላይ
መንቀሳቀሱን ቀጥለው ነበር።
ይህንን መሰረት በማድረግም ቁጥራቸው ከበፊቱ በዛ ያለ የፖለቲካ ቡድኖች
ተደራጅተው የተለያየ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይህም፣ ቀደም ሲል በሃገር ውስጥ
ለመንቀሳቀስ የሞከሩትን ህብረ ብሔራዊ ድርጅቶችን ጨምሮ አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶች
እና ሃገር ውስጥ በትጥቅ ትግል ይንቀሳቀሱ የነበሩ ‘ነጻ አውጭ ድርጅቶች’ ደጋፊ ቡድኖችን
ያካትታል። የነኚህን ድርጅቶች የተናጠል እንቅስቃሴዎች ለማቀናጀት የተለያዩ ጥረቶች
ቢደረጉም አካታች ለሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ባለው አናሳ አእምሮአዊ ዝግጁነት የተነሳ
ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። በዚህ አይነቱ፣ ሁሉም በየራሱ ጎጆ ተደራጅቶ እርስ በርሱ
22
በሚራኮትበት ሁኔታ እራሳቸውን በትጥቅ ትግል ያደራጁ ‘የነጻ አውጭ ድርጅቶች’
ተሳክቶላቸው ሃገሪቱን ሙሉ ለሙሉ ሊቆጣጠሩ ችለዋል። ኢህአዴግም፣ ከጅምሩ በህብረ
ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ በነበረው የጠላትነት ስሜት የተነሳ እንዲህ አይነቶቹ
ድርጅቶች ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገቡ ከገቡም ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ
22 እነኚህ ድርጅቶች ለትጥቅ ትግሉ የነበራቸው ጽኑ እምነት እና የከፈሉት መስዋዕትነት
እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በገዢው ሥርዓት ውስጥ የነበረው መፍረክረክ እና በዓመታት ውስጥ
የተጠናከረው የህዝብ ድጋፍ እጦት ለ 1983 ለውጥ መምጣት ከፍተኛውን ድርሻ አበርክቷል
ተብሎ ይታመናል።