Page 60 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 60
ደስታ መብራቱ
አፍራሽ ቅጥያዎች በመለጠፍ በህግ እንዲታገዱ ከመጠየቃቸው በፊት የሀገሪቱን ታሪካዊ እና
ተጨባጭ እውነታ በጥሞና መመርመሩ ይጠቅማቸዋል። በብሔር የመደራጀት ዋነኛው
ችግር የሚመነጨው፣ ማህበራዊ ማንነትን እንደ ብቸኛው የማንነት መገለጫ ከማድረግ እና
ይህንንም ለሃገረ መንግስት ምስረታ እንደ ዋነኛ መነሻ መሰረት አድርጎ ከመውሰዱ ላይ ነው።
እነኚህ በማህበራዊ ማንነት ላይ የተመረኮዙ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ እንዲሆኑ
ከተፈለገ ሰብዓዊ ማንነትን በሚያከብር እና ለዘመኑ በሚመጥን የዜግነት አመለካከት ሊቃኙ
ይገባቸዋል። ይህ ካልሆነ፣ በብዙዎቹ አንጋፋ የብሔር ድርጅቶች ውስጥ ባሁኑ ስዓት
እንደሚታየው ጠባብ ወደሆነ የመንደር እና የቤተሰብ መጠቀሚያነት መሸጋገራቸው እና
የግጭት እና ውድቀት ምንጭ መሆናቸው የማይቀር ይሆናል።
የሃገራችንን ፖለቲካ አካታች እና ፍትሃዊ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ለዘመናት
የተጠራቀሙትን የማንነት ቀውሶች በሃገራዊ አንድነት ማከም በጣም አስፈላጊ ያደርገዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ባጠቃላይ፣ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይ
በሃገሪቱ ገኖ የታየውን ‘የብሔር ፖለቲካ’ በሃገራዊ አንድነት መቃኘት ያሰፈልጋል። ይህ
እንዲሆን፣ በማህበራዊ ማንነት ላይ የተመረኮዘ ሃቀኛ ፖለቲካ የሚያራምዱ ቡድኖች
ጥያቄዎቻቸው በተሟላ ሁኔታ ሊመለሱ የሚችሉት ሰብዓዊ ማንነትን እና የዜግነት መብትን
በሚያካትት ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ መሆኑን መረዳት እና ይህንኑም ማክበር እና ማስከበር
ይኖርባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ህብረብሔራዊ ወይንም የዜግነት ፖለቲካ እናራምዳለን
የሚሉ የፖለቲካ ቡድኖችም፣ በዘመናት ውስጥ የተፈጠረውን የማንነት ቀውስ እና ከዚህ ጋር
ተያይዞ ያለውን የመንፈስ መጎዳት በመረዳት ይህንን ለመፈወስ የሚያስችሉ መፍትሔዎችን
ከብሔር ፖለቲካ አራማጆች ጋር በጋራ መሻት እና ለተግባራዊነቱም አብሮ መስራት
ይጠበቅባቸዋል። ይህንንም በማድረግ፣ ይበልጥ አሰባሳቢ እና አካታች ወደሆነ የፖለቲካ
ሥርዓት መሸጋገር ይቻላል።