Page 58 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 58
ደስታ መብራቱ
ከዚህ ተከትሎ የመጣው የኢህአዴግ መንግስት፣ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ
ያቆጠቆጠውን የብሔረሰቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶችን ለመተግበር የሚያስችሉ
ማእቀፎችን ለመመስረት ሙከራ አድርጓል። የህዝቦች ቋንቋ እና ባህል የሚከበርበት እና
ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት መንግስታዊ ሥርዓት መፍጠር እንደ ኢትዮጵያ
ላሉ የበርካታ የብሔረሰቦች ሃገር ዘላቂ ልማት እና እድገት አስፈላጊ መሆኑ ሊያከራክር
አይገባም። ነገር ግን፣ ኢህአዴግ የተከተለው መስመር የትናትናውን በደል ለመካስ
በሚመስል መልኩ፣ የሌሎችን ዜጎች በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል በነፃነት የመኖር መብት
ለመጣስ መጠቀሚያ በመሆኑ ቀደም ሲል የነበረውን አንድ ወጥ አሃዳዊነት በርከት ወዳለ
ብሔረሰባዊ አሃዳዊነት (Ethnicised Unitarianism) እንዲያመራ አድርጎታል።
በመሆኑም፣ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ በርካታ የሃገሪቱ ዜጎች
ኢትዮጵያዊነታቸውን ለሚያጠራጥር አዲስ አይነት የማንነት ቀውስ ተዳርገዋል። ይህ
ባንዳንድ የአፍሪካ ፖለቲካ ተንታኞች አደገኛ ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራ ለሃገራዊ አንድነት
መጠናከር የሚጠቅሙ እሴቶችን ለመሸርሸር የሄደበት አሳፋሪ መንገድም ሃገሪቱን ዛሬ
ላለችበት የፖለቲካ ቀውስ እና ራሱንም ለታሪክ ተወቃሽነት አብቅቷል። በጥቅሉ፣ የማንነት
ጥያቄ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በተግባር ላይ ከዋለው የፌደራል አወቃቀር ጋር በተያያዘም
ይበልጥ አወዛጋቢ ከሆኑ የፖለቲካ ጥያቄዎች አንዱ እና ዋነኛው እንዲሆን አድርጎታል።
ከዚያም አልፎ፣ ለበርካታ ወገኖች እልቂት እና በብዙ መቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን
መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።
ባለፉት ስልሳ አመታት የማንነትን ጥያቄ በተመለከተ የሚሰጡ ትንታኔዎች
በአብዛኛው በፖለቲካው መስክ ከሚታየው የተቀነበበ ትንተና ድክመቶች የነጹ ሊሆኑ
አልቻሉም። ይህም፣ ባንድ በኩል በሃገሪቱ ምንም አይነት የብሔር ጭቆና አልነበረም
ከሚለው እና ገሃድ የነበረውን የማንነት በደሎች በሃገራዊ አንድነት ለመሸፈን ከሚደረግ
ሰጎናዊ አቋም አንስቶ፣ ፍትሃዊ የሆነውን የብሔሮችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት
እስከ መገንጠል ድረስ በሚለጥጠው ተስፈንጣሪ የግራ ዘመም አቋም ይገለጻል። ከምህዳራዊ
አስተሳሰብ አኳያ፣ የማንኛውም ሰው ማንነት የበርካታ ጥምር መለያዎች መስተጋብር እንጂ
በአንድ የተናጠል ባህርይ የሚገለጽ አይደለም። በዚህም መሰረት፣ የማንኛውም ሰው ማንነት
በመሰረታዊነት በሚከተሉት ሶስት ዋነኛ የማንነት ጥምር መስተጋብር የሚገለጽ ይሆናል።
የመጀመሪያው ዓብይ ማንነት፣ የተፈጥሮ ማንነት (natural identity) ሲሆን
ይህም የሰው ልጅ ከእንስሳቱ ዓለም የሚለየውን ሰብዓዊ ባህርይ የሚያጎናጽፈው
ተፈጥሮዋዊው የዘረ መልእ ማንነቱ ነው። በዚህም ማንነቱ የተነሳ ሁሉም የሰው ልጅ
በሰውነቱ የሚጎናጸፈው መሰረታዊ ባህሪያት እና መብቶች ይኖሩታል። ይህ የተፈጥሮ
ማንነት የማናቸውም ማንነት መነሻ መሰረት በመሆኑ የሉላዊነት (universality) ባህሪ
አለው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት፣ በተባበሩት መንግስታት የጸደቀው ሉላዊ
የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) በዚሁ የሰው
ልጆች ሰብዓዊ ማንነት እና ተያያዥ መብቶቻቸው ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም፣
ለበርካታ አባል ሃገራት ህገ መንግስት እንደመነሻ ግብዓት በማገልገል ላይ ይገኛል። በጥቅል