Page 56 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 56
ደስታ መብራቱ
መሰረት ማበርከቱ አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ፣ በተከታታይ ነገሥታት የተከናወኑት የሃገረ
መንግሥት ግንባታ ሂደቶች በኢኮኖሚያዊ ትስስር እና ልማት ላይ የተመረኮዘ ሃገራዊ
አንድነት ላይ ከማተኮር ይልቅ አንድ ወጥ አሃዳዊነትን በሚያጠናክሩ ተቋማዊ እርምጃዎች
እና ተጽእኖዎች ላይ በማተኮሩ ለበርካታ የማንነት ቀውሶች ምንጭ ሊሆኑ ችለዋል።
ለዚህም፣ ቋንቋና ሃይማኖቶች እንደ ዋነኛ መሳሪያ ማገልገላቸውን የሚያመላክቱ
በርካታ የታሪክ መረጃዎች አሉ። ይህም ለዘመናት፣ በተለይም በአማርኛ እና በኦሮምኛ
እንዲሁም በክርስትና እና በእስልምና መካከል የነበረውን መገፋፋት እና መወራረስ
መመልከት ይቻላል። በዘመነ ዓጼ ኃይለ ሥላሤ ይህ የአሃዳዊነት ሂደት ከፍተኛ ተቋሟዊ
ቅርጽ እየያዘ ለመምጣቱ በርካታ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል። ለምሳሌም ያህል፣ ለበርካታ
ዓመታት በሀገሪቱ ብቸኛ በሆነው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ለመማር
የአማርኛ ፈተናን ማለፍ ግዴታ ነበር። አንድን ቋንቋ እንደሃገራዊ የመግባቢያ ቋንቋ እስከ
ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ማስተማሩ አስፈላጊ መሆኑ ባይካድም፣ በዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሂደት
ውስጥ ምንም አይነት አስተዋጽኦ የማይኖረውን እና ለብዙዎች ሁለተኛ ቋንቋ የሆነውን
ካላለፍክ ብሎ የአንድን ዜጋ የመማር መብት መከልከል የሚፈጥረው የተጎጂነት ስሜት ቀላል
አይደለም።
ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ገና ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡም
ሆነ ስራ በሚቀጠሩበት ጊዜ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተሰጣቸውን መጠሪያ ስም
እንዲቀይሩ ይገደዱ እንደነበር የሚነገሩ ትርክቶችም አሉ። እዚህ ላይ፣ ታላቁ የአማርኛ
ሥነጽሁፍ ሊቅ እና ባለቅኔው ኦቦ ፀጋዬ ገብረመድህን የዚሁ ተጽእኖ ሰለባ እንደነበር
መግለጹ በቂ ነው። ይህና ሌሎች ከቋንቋ ጋር የተያያዙ ተቋሟዊ ጭቆናዎች በአፍሪካ ውስጥ
ብቸኛ የሆነ የራሱ የጽሁፍ ሥርዓት ባለው የአማርኛ ቋንቋችን መኩራት ሲገባን በርካቶች
እንደመጨቆኛ መሳሪያ እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል። ለአስተዋይነታቸው ምስጋና ይግባው
እና፣ ኦቦ ፀጋዬን እና ጋሽ ስብሐትን የመሰሉ በርካታ የሥነ ጽሁፍ ሰዎች እንደዘመኑ
አንዳንድ ፖለቲከኞች አማርኛን አትናገሩ ከማለት በተቃራኒው ቋንቋውን ይበልጥ
አበልጽገውት እና አዳብረውት አልፈዋል።
ወደ ሃይማኖቱ ስንመጣ፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከመካ ውጭ ሁለተኛዋ እስልምና
የተሰበከባት እና የተመለከባት ሃገር ብቻ ሳትሆን ያለ እርሷ ከለላ እና ድጋፍ ምናልባትም
እስልምና ዛሬ ለደረሰበት ደረጃም ላይደርስ ይችል ነበር ተብሎ ይነገራል። ይህም በመሆኑ፣
በነኚህ ሁለት ታላላቅ ሃይማኖቶች መካከል አልፎ አልፎ የመገፋፋት ግጭት ቢኖርም
በአብዛኛው ለዘመናት የዘለቀ መወራረስ እና መተሳሰርን ፈጥሯል። ይህ ሁኔታ በአብዛኛው
ማህበረሰባችን ውስጥ የሚታይ ሲሆን በተለይም በቀድሞው የወሎ ክፍለ ሃገር ውስጥ
እጅግ በሚያስገርም ሁኔታ ጎልቶ ይገኛል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተከታታይ ነገሥታት
ከክርስትና እምነት ጋር ከነበራቸው ጥብቅ ትስስር የተነሳ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች
የተለያዩ የአድሎአዊነት በደሎችን ሲያስተናግዱ ኖረዋል። ይህ አድሎአዊነት
በመጨረሻዎቹ ነገሥታት ዘመን ይበልጥ ተቋማዊ ቅርጽ ሊይዝ ችሏል።