Page 51 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 51

ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ


                     በሶስተኛ  ደረጃ፣  ምንም  እንኳን  በስፋት  ባይነገርላቸውም፣  በጠረፍ  አካባቢ
             የሚኖሩ ህዝቦች ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር የነበራቸውን ቁልፍ ድርሻ በመገንዘብ
             ሁሉም  የፖለቲካ  ድርጅቶች  የዳር‐መሃል  የሚባለውን  ፖለቲካዊ  ዘይቤ  ለአንዴ  እና
             ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ማስወገድ ይኖርባቸዋል። ይህ ሊሆን
             የሚችለው፣ የዳርቻው አካባቢ ማህበረሰቦች ሃገሪቱን ወደ መሃል የሚያሰባስበው ሃይል
             (centripetal force) አካል ሆነው መሃሉ በብዙ መልኩ ዳሩንም መምሰል ሲጀምር ነው።
             ያለ ዳሩ መሃል የሚባል ነገር እንደማይኖር መረዳትም ለዚህ ሂደት ይጠቅማል።

                     ይህ  ዳሩን  ወደ  ማዕከል  የማምጣት  ፖለቲካ  ለዘመናት  የነበረውን  የመብት
             መዛባት ከማስተካከልም በላይ ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ ለሃገራችን የፖለቲካ ሽግግር
             ልዩ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። የዚህ ዋነኛው ምክንያት፣ በነኚህ አካባቢዎች የሚኖሩ
             አብዛኛዎቹ  ማህበረሰቦች  የሌሎቹን  ያህል  በሃገራችን  ፖለቲካ  መሰረታዊ  ህመሞች
             ያልተተበተቡ ከመሆናቸውም በላይ የፖለቲካ ልሂቃኖቻቸውም ከሃገር በቀል እውቀቶች
             እና ሥርዓቶቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት በሚመለከት እንደ አብዛኞቻችን ጠቅልለው
             ያልተፋቱ መሆናቸው ነው። ለዚህም ማረጋጋጫ የሚሆኑን፣ ከቦረና እስከ አፋር፣ ከጋሞ
             እስከ  ሶማሊ  ያሉ  ማህበረሰቦች  ያላቸው  የተሻለ  የማድመጥ  እና  የመደማመጥ  ባህል፣
             ውጤታማ የሆኑ የግጭት አፈታት ዘዴዎቻቸው፣ እና ማህበራዊ ርትዕን የሚያሰፍኑበት
             የዳኝነት ሥርዓቶቻቸው ናቸው።
                     እነኚህ  ማህበራዊ  ክህሎቶች  እና  እሴቶች  በጥርጣሬ  እና  በበላይነት  ስሜት
             የተተበተበውን  የመሃል  ሃገር  ፖለቲካ  በመጠኑም  ቢሆን  ለማለዘብ  እና  ለማስከን
             እንደሚያግዙ የሚያመላክቱ ወጣት የፖለቲካ መሪዎችም ከነኚሁ አካባቢ ወጥተው ማየት
             ጀምረናል። እዚህ ላይ፣ እነኚህ ሃገር በቀል እውቀቶች እና ሥርዓቶች በዘመኑ የፖለቲካ
             ህመም  የተነሳ  ለመሸርሸር  አደጋ  እየተጋለጡ  መሆናቸውን  መገንዘብ  ያስፈልጋል።
             ስለዚህም፣  ጊዜው  ሳይረፍድ  ከእነኚህ  ሃገር  በቀል  እውቀቶች  እና  ሥርዓቶች  ሊወሰዱ
             የሚችሉ ጠቃሚ ልምዶችን በተቀናጀ እና በተደራጀ መልኩ አጥንቶ የፖለቲካ ባህላችን
             እና ሥርዓታችን አካል እንዲሆኑ ማድረግ ለሃገራዊው የፖለቲካ ሽግግር ጤናማነት ትልቅ
             አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል። በዚህ ረገድ፣ በሃገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት
             ተቋማት፣  የማህበራዊ  ሳይንስ  ምሁራን  እና  በዚህ  መስክ  የሚንቀሳቀሱ  ሃገር  በቀል
             ድርጅቶች ጉልህ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል ይታመናል።
                      በአጠቃላይ፣ ከምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎች አኳያ፣ በማንኛውም ምህዳር
             ውስጥ  የሚገኙ  ክፋዮች  ምንም  ያህል  አናሳ  ቢሆኑ፣  እንደ  ምሉዕነታቸው  ለአጠቃላዩ
             ምህዳር ጤናማነት እና ዘላቂነት የራሳቸው የሆነ ድርሻ አላቸው። የተፈጥሮ ምህዳሮቻችንን
             ብንመለከት፣ ከትንሽቷ ህዋስ አንስቶ አስከ ታላቁ ሰው የየራሳቸው ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸው
             ነው የምናየው።  በተመሳሳይም፣ በሃገራችን ውስጥ ያሉ ማህበረሰቦች፣ ምንም ያህል አናሳ
             ቢሆኑ  በኢትዮጵያ ውስጥ  ለሚኖረው  የፖለቲካ  እና  ኢኮኖሚ ምህዳር  ጤናማነት እና
             ዘላቂነት የራሳቸው የሆነ ድርሻ እንደሚኖራቸው መገንዘብ ይገባል።

                                                                        43
   46   47   48   49   50   51   52   53   54   55   56