Page 47 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 47
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
የፌደራላዊ ሥርዓቱ ውጤታማነት ሊለካ የሚገባው፣ ማንኛውም ሰው በሰውነቱ ሊኖረው
የሚገባውን መሰረታዊ የመኖር እና በአካልም በመንፈስም የመበልፀግ ህገ መንግሥታዊ
መብቶች ከቡድናዊ መብቶች መከበር ጋር አጣጥሞ መተግበር በመቻል አቅሙ ነው።
በዚህ ረገድ፣ አሁን ያለው የፌዴራል አወቃቀር ለብሔሮች ራስን በራስ
የማስተዳደር መብት መከበር መሰረት የጣለ ቢሆንም በህገመንግስቱ ውስጥ የተደነገጉትን
መሰረታዊ ሰብዓዊ መብት ለሚጥስ አተገባበር እድል የሚሰጥ ሆኖ በመቀረጹ ለበርካታ
የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የመልካም አስተዳደር ጉድለት ምንጭ ሆኗል። ከዚህም
በተጨማሪ ያንዳንድ ክልሎች አከላለል ውጤታማ የልማት አስተዳደርን ለመተግበር
አመቺ አለመሆንም ይታያል። ስለዚህም፣ የተሻለው አማራጭ ያለው የፌዴራል አወቃቀር
ያሉበትን የአካታችነት እና ልማታዊ ውጤታማነት ውሱንነት በሂደት በማሟላት
ለዘለቄታው የሀገሪቱ ልማት እና የህዝቦች ብልጽግና እንዲያገለግል ማድረግ ይሆናል።
ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት መሰረታዊ መዋቅራዊ ችግሮች አንዱ ከሌላው በእጅጉ የተሳሰሩ
በመሆናቸው አንደኛውን በተናጠል ለመፍታት በመሞከር ወደ ዘላቂ መፍትሔ ማምራት
እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል።
በቀዳሚው ክፍል እንደተጠቀሰው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ዋነኛ
ተዋንያን ነን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአጠቃላይ የሃገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር አካል
ናቸው። ይህም ማለት፣ አንዱ ፓርቲ ከሌላው ፓርቲ ጋር የሚኖረው መስተጋብር ባጠቃላይ
የምህዳሩን ጤናማነት ይወስነዋል። በመሆኑም በማንኛውም ወቅት ለሚፈጠር የፖለቲካ
ቀውስ፣ (የድርሻ ማነስ ወይም መብዛት ካልሆነ በስተቀር) የትኛውም ፓርቲ ከደሙ ንጹህ
ነኝ ማለት አይችልም። ከዚህ አኳያ፣ ለህዝቦች መብት እና ዘላቂ የልማት ፍላጎት መሟላት
ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት ለህዝቦች ልዕልና ተገዢ
በመሆን፤ ዋነኛ የሆኑት መዋቅራዊ የፖለቲካ ችግሮችን እውቀት ላይ በተመረኮዘ ሂደት
ሊፈቱ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር እና በተግባር ላይ ማዋል ነው።
39