Page 42 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 42
ደስታ መብራቱ
ሊያረጉ አልቻሉም። በዚህ ረገድ የሃገሪቱ ምሁራን እና የሚዲያ ሰዎች ባንድ
አቅጣጫ የተቀነበበ ትንተና (linear thinking) ላይ የተመረኮዘ ፖለቲካዊ
ትንተናዎች ከመስጠት መታረም እና ዙሪያ መለስ እይታ ሊሰጥ በሚችለው
ምህዳራዊ አስተሳሰብ ለመታነጽ ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል።
ix. ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን አበይት ህመሞች እና ሌሎችንም በጥልቀት ፈትሾ
መድሃኒት መሻት የሀገሪቱን ፖለቲካ ወደበሰለ እና የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት
ለማሸጋገር የመጀመሪያው አስፈላጊ እርምጃ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሂደት
ለፖለቲካ መሪዎች ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በእውቀት
እና አስተውሎት ላይ ለተመረኮዘ ውይይት እና መግባባት የየበኩላቸውን
አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
x. በምህዳራዊ አስተሳሰብ መሰረት፣ ማንኛውም ምህዳር በአንድ ተመሳሳይ ወቅት
በራሱ ምሉእ (whole) ሆኖ የሚቆም ሲሆን በተመሳሳይ ወቅት የሌላ ከፍ ያለ
ምህዳር ደግሞ ክፋይ አካል (part) ነው። በዚህ መሰረት ክፋዮች የማንኛውም
ምሉእነት መሰረቶች ሲሆኑ እነኚህ ምሉዕነቶች ግን ከክፋዮቹ ተደማሪነት በላይ
የሆነ ህልውና ይኖራቸዋል። በክፋይነት እና ምሉዕነት መርህ መሰረት፣
እንደኢትዮጵያ ባሉ የበርካታ ብሔረሰቦች ሃገር ውስጥ አካታች እና ውጤታማ
የሆነ ሥርዓተ መንግስት ለመገንባት የእያንዳንዱን ብሔረሰብ ምሉዕነት
ከሀገራዊው ልዕልና ጋር የሚያጣጥም የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት የግድ
ይሆናል።
xi. ሌላው የምህዳራዊ አስተሳሰብ መርህ፣ ሁሉም እውነቶች አንጻራዊ እንደሆኑ እና
አንድ እውነታ (reality) ከአንድ በላይ በሆኑ (multivalent) እውነቶች ሊገለጽ
እንደሚችል ያመላክታል። የሃገራችን ፖለቲካ አንዱ ልዩ መገለጫ፣ አብዛኞቹ
ፖለቲከኞቻችን ሌላው ወገን አለኝ የሚለውን እውነት ለማዳመጥ ዝግጁ
አለመሆን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን ‘እውነት’ በሌላው ላይ በኃይል ለመጫን
በሚሄዱበት ርቀትም ነው። ከዚህ በሽታ ለመላቀቅ ብዙዎቹ ፖለቲከኞቻችን
በከፍተኛ ደረጃ ከተጠናወታቸው ‘የእኔ ብቻ እውነት’ ከሚለው አመለካከት
ነጽተው የሌላውንም ወገን ‘እውነት’ ለመስማት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
xii. ከሃገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በጥብቅ የሚተሳሰረው ሌላው ዓብይ መርህ
በብዝሃነት እና ምህዳራዊ መረጋጋት (stability) መካከል ያለውን ግንኙነት
ይመለከታል። በዚህ መርህ መሰረት፣ በማንኛውም ምህዳር ውስጥ የሚኖረው
ብዝሃነት ወደ ተሻለ ሥርዐት ለመሻገር የሚያስችል መወራረስ እና መዳቀል
ከማሳለጡም በላይ ምህዳራዊ መረጋጋትን እና ሚዛናዊነትን ለማረጋጋጥ
ያግዛል። ከዚህ አኳያ፣ በሃገራችን የሚገኘው የሥነ-ምህዳር፣የቋንቋ፣ የባህል፣ እና
የሃይማኖት ብዝሃነት ለሃገሪቱ ቀጣይ እና ዘላቂ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው
መሰረት ሊሆን እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል። ይህ ግን ሊሆን የሚችለው
የነኚህን ብዝሃነት ጠቀሜታ ባግባቡ ተረድቶ የእርስ በርስ ተደጋጋፊነታቸውን
እና ተወራራሽነታቸውን በሚያጠናክር ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ሲደገፉ ብቻ
ነው።