Page 37 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 37
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
13
2.2 የምህዳራዊ አስተሳሰብ ዓበይት መርሆዎች
ቀደም ባለው ክፍል፣ ምህዳራዊ አስተሳሰብ የሃገራችንን የፖለቲካ ህመሞች
በአግባቡ ለመረዳት የሚኖረውን አስተዋጽኦ በመግለጽ በዚሁ እይታ ልዩ ትኩረት
ሊሰጣቸው የሚገቡ ዋነኛ የፖለቲካ ህመሞቻችንን ለማመላከት ተሞክሯል። በዚህ ክፍል
ከምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎች መካከል ለሃገራችን የፖሊቲካ ህመሞች ፈውስ ለማግኘት
ይረዳሉ ከሚባሉት አበይቶቹን እንዳስሳለን። እነኚህ መርሆዎች በማንኛውም የተፈጥሮ፣
ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ እና ፖለቲካዊ ምህዳሮች ላይ ሊተገበሩ የሚችሉ መሰረታዊ
መርሆዎች በመሆናቸው አንባቢዎች በግልም ሆነ በሙያ ህይወታቸው ሊጠቀሙባቸው
ይችላሉ።
ክፋይነት እና ምሉእነት፡ በምህዳራዊ አስተሳሰብ መሰረት፣ ማንኛውም ምህዳር
በአንድ ተመሳሳይ ወቅት በራሱ ምሉእ (whole) ሆኖ የሚቆም ሲሆን በተመሳሳይ ወቅት
የሌላ ከፍ ያለ ምህዳር ደግሞ ክፋይ አካል (part) ነው። በዚህ መሰረት ክፋዮች የማንኛውም
ምሉዕነት መሰረቶች ሲሆኑ እነኚህ ምሉዕነቶች ግን ከክፋዮቹ ተደማሪነት በላይ የሆነ ልዕልና
ይኖራቸዋል። በተጨማሪም፣ በአንድ ምህዳር ውስጥ በሚኖሩ ክፋዮች መካከል የሚኖረው
የማያቋርጥ መስተጋብር በአጠቃላይ በምሉዕ ውስጥ ለሚኖረው መሰረታዊ ለውጥ ዋነኛው
ምንጭ ስለሆነ በክፋዮቹ መካከል ያለውን መስተጋብር በጥልቀት መረዳት፣ ምሉዕ ምህዳሩን
በአግባቡ ለመረዳት እና ለመምራት ቁልፍ ጉዳይ ነው።
ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በአንድ ቤተስብ ውስጥ ያሉ አባላት እያንዳንዳቸው
ራሳቸውን የቻሉ ምሉእ ሰው ሲሆኑ፣ ቤተስብ የተባለው ከፍ ያለ ምሉእ ምህዳር ደግሞ
ክፋይ ናቸው። ነገር ግን፣ ቤተስብ በደፈናው የሰዎች ስብስብ ሳይሆን በያንዳንዱ የቤተስብ
አባል መካከል በሚኖረው መስተጋብር እና መተሳሰር የሚገለጽ ምህዳር ነው። ስለሆነም
አንድን ቤተስብ በአግባቡ ለማስተዳደር፣ እያንዳንዱን የቤተስብ አባል እንደምሉእ ሰውነቱ
መረዳት እና በሁሉም የቤተስብ አባላት መካከል የሚኖረውን መስተጋብር በአግባቡ
መገንዘብ እና መያዝ ይጠይቃል። በተመሳሳይ፣ ቤተሰቦች ወደ ማህበረሰብ፣ ማህበረሰቦች
ወደ ብሔረሰብ፣ ብሔረሰቦች ደግሞ ከሁሉም ከፍ ያለ ልዕልና ወዳለው ሃገረሰብ ያድጋሉ
ማለት ነው። በክፋይነት እና ምሉዕነት መርህ መሰረት፣ እንደኢትዮጵያ ባሉ የበርካታ
ብሔረሰቦች ሃገር ውስጥ አካታች እና ውጤታማ የሆነ ሥርዓተ-መንግስት ለመገንባት
የእያንዳንዱን ብሔረሰብ ምሉእነት ከሀገራዊው ልዕልና ጋር የሚያጣጥም የፖለቲካ ሥርዓት
መገንባት የግድ ይሆናል።
13 የዚህ ክፍል አብዛኛው፣ ሐምሌ 18 ቀን 2012 በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ የተነበበ ነው።
29