Page 38 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 38

ደስታ መብራቱ


                  አንፃራዊ  ዕውነት፡  በዚህ  መርህ  መሰረት፣  ሁሉም  ምህዳሮች  ቀጣይ  በሆነ
           የለውጥ ሂደት ውስጥ ስለሆኑ ሁሉም እውነቶች አንጻራዊ ከመሆናቸውም በላይ አንድ
           እውነታ  (reality)  ከአንድ  በላይ  በሆኑ  (multivalent)  እውነቶች  ሊገለጽ  ይችላል።
           በዚህም የተነሳ፣ አብዛኛው ገሃዱ ዓለም በግራጫው ማእቀፍ (grey-zone) ውስጥ የሚገኝ
           ሲሆን ጥቁር ወይም ነጭ እውነታ ቅጽበታዊ የሽግግር ሁነት (Transient state) መገለጫ
           ብቻ ነው። በሳይንሱ ዓለምም ያለው እውነት በአብዛኛው አንጻራዊ ሲሆን፣ ፍጹም እውነት
           የሚገኘው በሂሳባዊው ቀመር (mathematical models) ውስጥ ብቻ ነው። ይህ ዕውነታ፣
           በተለይም እጅግ ተለዋዋጭ በሆነ የፖለቲካ ምህዳር ላይ ገኖ የሚታይ ባህርይ በመሆኑ
           ይህንን  መገንዘብ  የአንድን  የፖለቲካ  ማህበረሰብ  ጤናማነት  ሊወስኑ  ከሚችሉ  ዓበይት
           ጉዳዮች ዋነኛው ነው።
                  የሃገራችን ፖለቲካ አንዱ ልዩ መገለጫ፣ አብዛኞቹ ፖለቲከኞቻችን ሌላው ወገን
           አለኝ የሚለውን እውነት ለማዳመጥ ዝግጁ አለመሆን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን ‘እውነት’
           በሌላው ላይ በጉልበት ለመጫን በሚሄዱበት ርቀትም ነው። እንዲህ አይነቱ አመለካከት
           ከ1960ዎቹ ጀምሮ እሰከ አሁን ድረስ ከፍተኛ ዋጋ ሲያስከፍለን ቆይቷል። ከዚህ በሽታ
           ለመላቀቅ ብዙዎቹ ፖለቲከኞቻችን በከፍተኛ ደረጃ ከተጠናወታቸው ‘የእኔ ብቻ እውነት’
           ከሚለው  አመለካከት  ተላቀው  የሌላውንም  ወገን  ‘እውነት’  ለመስማት  ዝግጁ  መሆን
           ይጠበቅባቸዋል።  ይህንንም በማድረግ፣ አንድን ጉዳይ ከተለያየ አቅጣጫ በመመልከት እና
           በመረዳት ለእውነታው በይበልጥ የሚቀርብ መግባቢያ ሃሳብ ላይ መድረስ እና ለፖለቲካ
           ችግሮቻችን ተስማሚ የሆኑ መፍትሔዎችን ማመንጨት ይቻላል።
                  ብዝሃነት  እና  ምህዳራዊ  መረጋጋት  (stability)፡    በዚህ  መርህ  መሰረት፣
           ብዝሃነት (diversity) የማንኛውም ምህዳር የመረጋጋት እና የዘላቂነት ዋነኛ መነሻ ምንጭ
           ነው። ይህም ማለት፣ በማንኛውም ምህዳር ውስጥ የሚኖረው ብዝሃነት ወደ ተሻለ ሥርዓት
           ለመሻገር የሚያስችል መወራረስ እና መዳቀል ከማሳለጡም በላይ ምህዳራዊ መረጋጋትን
           እና  ሚዛናዊነትን  ለማረጋጋጥ  ያግዛል።  ከዚህ  በተቃራኒው፣  በአንድ  ወጥነት
           (monocultural)  ላይ  የተመረኮዘ  ምህዳር  ለመውደቅ  (crash)  እና  ከዚህም  ከከፋ
           ለመጥፋት (extinction) አደጋ የተጋለጠ ይሆናል። ከዚህ አኳያ፣ በሃገራችን የሚገኘው
           የሥነምህዳር፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ እና የሃይማኖት ብዝሃነት ለሃገሪቱ ቀጣይ እና ዘላቂ እድገት
           ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሰረት ሊሆን እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል። ይህ ግን ሊሆን
           የሚችለው የነኚህን ብዝሃነት ጠቀሜታ ባግባቡ ተረድቶ የእርስ በርስ ተደጋጋፊነታቸውን
           እና ተወራራሽነታቸውን በሚያጠናክር ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ሲደገፉ ብቻ ነው። ከዚህ
           በተቃራኒው፣  በአሃዳዊነት  ወይንም       አሁን  ባንዳንድ  የክልል  ፖለቲካ  አራማጆች
           እንደሚታየው  ‘ራስን  በራስ  ማስተዳደር’  በሚል  ሽፋን  ‘አንድ  ወጥነትን’  ለመፍጠር
           የሚደረገው ጥረት ያንኑ ማህበረሰብ በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዳው እና ከከፋም ሊያጠፋው
           እንድሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል።
   33   34   35   36   37   38   39   40   41   42   43