Page 43 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 43
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
xiii. የማንኛውም ምህዳር ውጤታማነት እና ዘላቂነት የሚወሰነው በክፋዮቹ መካከል
ለሚኖረው ትብብር እና ፉክክር በሚኖረው አያያዝ ውጤታማነት መሆኑ ሌላው
የምህዳራዊ አስተሳሰብ ዓብይ መርህ ነው። በክፋዮቹ አካላት መካከል
የሚኖረው ትብብር የምህዳሩን አሰራር ውጤታማነት እና መረጋጋት
(efficiency and stability) የሚወስን መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን በነኚሁ ክፋዮች
መካከል የሚኖረው ፉክክር እና ውድድር ደግሞ ለምህዳሩ ቀጣይ እድገት
አስፈላጊ ለሆነው ፈጠራ (innovation) ዋነኛ መሰረት ነው።
xiv. በዚህ መሰረት፣ በአንድ ሃገር ውስጥ የሚኖረው የፖለቲካ ምህዳር ጤናማነት
የሚወሰነው በፓርቲዎች መካከል ሊኖር በሚገባው የመተባበሪያ ማእቀፍ (ህገ
መንግስት እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓት) ጥንካሬ እና በመወዳደሪያ ሜዳው
አካታችነት ይሆናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ምስቅልቅል አንደኛው
ምንጭ ይህንን ሃገራዊ የመተባበሪያ ማዕቀፍ ከፓርቲዎች የመወዳደርያ
ፕሮግራም ጋር ከማደበላለቅ የሚመነጭ ነው።
xv. በተመክሮአዊ መማማር (adaptive learning) መርህ መሰረት፣ ውጤታማ
ተመክሮአዊ የመማማር ስርአት ያለው ምህዳር ያልተቋረጠ እና ቀጣይነት ያለው
ሽግግር ለማረጋገጥ ከፍተኛ አቅም ይኖረዋል። ይህም ማለት፣ ጠቃሚ
መረጃዎችን በሥርዓት የሚያደራጅ፣ የሚያጠራቅም እና ካንድ ትውልድ ወደ
ሌላው ትውልድ የሚያሸጋግር ምህዳር ላለተቋረጠ እና ቀጣይ ለሆነ ሽግግር ጥሩ
መሰረት ይኖረዋል። በዚህ ረገድ፣ ከሃገር በቀል የእውቀት ሥርአቶች
ልንወስዳቸው የምንችላቸውን ጠቃሚ ትምህርቶች እና ከዘመናዊው ፖለቲካችን
የምናገኛቸውን በጎም ሆነ ክፉ ተመክሮዎች በቅንነት በመማር ወጣቱ ትውልድ
በበጎው ተመክሮ ላይ በመገንባት ጎጂ ታሪካችንን ላለመድገም ብርቱ ጥረት
ማድረግ ይኖርበታል።
xvi. እስከ አሁን ድረስ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች የሚጠቆሙ መፍትሄዎች
በአብዛኛው ወይ በአንድ ክፍል ወገናዊነት ላይ የተመረኮዙ ምሉዕነት የጎደላቸው
ይሆናሉ ወይም ሁሉንም ዝርዝር ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ ለመመለስ
በሚያደርጉት ጥረት መያዣ መጨበጫው የጠፋበት የመፍትሄ ሃሳብ ሆነው
ይገኛሉ። ከዚህ ይልቅ፣ ላለንበት ውስብስብ ሁኔታ ሁለንተናዊ መፍትሔ
ለማግኘት ከተናጠል ሁነቶች (events) እና ድግግሞሽ (patterns) ባሻገር
በመመልከት የአመለካከት እና መዋቅራዊ ችግሮችን መመርመር በርካታ
ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ ልዩ ቋጠሮዎችን (dynamic knots) መፍታት
ይቻላል።
xvii. በዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱትን ያስተሳስብ ለውጦች በማምጣት እና ከዚህ
በላይ የተዘረዘሩትን የምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎችን በተቀናጀ መልኩ
ተግባራዊ በማድረግ አብዛኞቹን መሰረታዊ የፖለቲካ ህመሞቻችንን ማከም እና
የወደፊቱን የሃገራችንን የፖለቲካ ምህዳር በጤናማ መሰረት ላይ ለመገንባት
ይቻላል። በዚህ ሂደት ውስጥ፣ አንድን ውስብስብ ሁኔታ ለመፍታት ካንድ በላይ
የመፍትሔ መንገዶች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገንዘብም ይገባል።
35