Page 48 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 48
ደስታ መብራቱ
15
3.2 ዳሩን መሃል የማድረግ ፖለቲካ
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ሊኖራቸው ይችላሉ ተብለው
የሚገመቱ የፖለቲካ ቡድኖች እና የህብረተሰብ ክፍሎች በተወከሉበት እና በ 2011 በተካሄደ
አንድ ዓውደ ርእይ ላይ በአስተባባሪነት የመሳተፍ እድል አጋጥሞኝ ነበር። በዚህ ወቅት
ከተካሄዱ የቡድን ውይይቶች በአንደኛው፣ አንድ ተሳታፊ ‘የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛው
ችግር በአማራው፣ በኦሮሞው እና በትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን (elites) መካከል ያለው
የበላይነት ፉክክር ነው’ የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። ይህን በማስከተል፣ በምስራቃዊው
የሃገራችን ክፍል የሚገኝ አንድ የፖለቲካ ድርጅትን ወክለው የመጡ ሌላ ተሳታፊ ‘ችግሩ
ይህ መሆኑን ከተረዳችሁ ለምን ለተወሰኑ ዓመታት ሥልጣኑን ለእኛ ለቃችሁልን ሃገር
እንዴት እንደሚመራ አናሳያችሁም’ የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። በወቅቱ፣ እነኝህ አስተያየቶች
ብዙም ትኩረት ሳይሰጣቸው እና ቀጣይ ውይይት ሳይካሄድባቸው ታልፈዋል። በዚህ ፀሃፊ
እምነት፣ እነኚህ አስተያየቶች በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ ካሉት እና ትኩረት ሊሰጣቸው
ከሚገቡ ዋነኛ መዋቅራዊ ችግሮች አንዱ የሆነውን የመሃል እና ዳር (centre-periphery)
ፖለቲካን የሚያመላክቱ ናቸው። በዚህ ከፍል፣ ከላይ የተጠቀሱት አባባሎች ያላቸውን
መልእክት ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ በመተንተን ዳሩን ማዕከል የሚያደርግ ፖለቲካ
ለኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚኖረውን በጎ አስተዋጽኦ ለማመላከት ይሞከራል።
ወደ ወቅቱ የሃገራችን ፖለቲካ ከመግባታችን በፊት ግን ይህ የዳር እና መሃል
ፖለቲካ ከዚህ ቀደም በነበሩ የፖለቲካ ሥርዓቶች እንዴት ይታይ እንደነበር በአጭሩ
እንመለከታለን። ከዘመነ መሳፍንት በኋላ የነበረውን የሃገር ምስረታ ታሪክ ስንመለከት፣
የሌሎች ማህበረሰቦች አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከአማራ፣ ከትግራይ እና ከኦሮሞው
የወጡ ነገስታቶች እና የጦር አበጋዞች የመሪነቱን ድርሻ ይወስዳሉ። ወደ አጼ ኃይለሥላሴ
ዘመን ስንመጣ፣ የንጉሳዊው አገዛዝ መንግስታዊ መዋቅር በአብዛኛው ከላይ በተጠቀሱት
የአማራ፣ ኦሮሞ እና ትግራይ መኳንንቶች እና ልሂቃን የተሞላ እንደነበር የታሪክ መዛግብት
ያረጋግጣሉ። ከዚህ በተጨማሪም፣ ከሰሜናዊው እና ከመሃከላዊው የሃገራችን ክፍል ውጪ
ያለው አብዛኛው የሃገራችን ክፍል ዳር ሃገር በሚል አጠራር ውስጥ የሚጠቃለል ነበር።
በነዚህ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚመደቡ ገዢዎችም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የነበሩትን
ባላባታዊ አስተዳደሮች ከማቆየት ውጭ፣ በአብዛኛው ከነኚሁ ሶስት ብሄረሰቦች በተለይም
ከአማራው ወገን እንደነበሩ ይታወቃል።
ከዚህም አልፎ፣ ንጉሡ ስልጣናቸውን በመቀናቀን ወይም ለመጋፋት በመሞከር
የሚጠረጥሯቸውን መኳንንት እና ልሂቃን በሹመት ስም ወደ እነኚህ የሃገሪቱ ክፍሎች
ይመድቡ እንደነበር የሚነገሩ ትርክቶችም ነበሩ። ከልሂቃኖቹ ሹመቶች መካከል የ1953
መፈንቅለ መንግስት ጠንሳሽ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአቶ ገርማሜ ንዋይ የወላይታ እና
የጅግጅጋ ሹመት እና በተመሳሳይ መልኩ ፍጹማዊ የንጉሥ አገዛዝ በመተቸት የታወቁት
15 የዚህ ክፍል አብዛኛው፣ ነሐሴ 16 ቀን 2012 በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ታትሟል።