Page 46 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 46
ደስታ መብራቱ
ሥርዓቶች ካንዱ ወይንም ከሌላው ከወረሱት በሽታዎች ነጻ ሊሆኑ አልቻሉም። ከዚህ
በተጨማሪም፣ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ይዞት ከመጣው በርካታ ፈተናዎች እና እድሎች
አኳያ አብዮታዊ ዲሞክራሲም ሆነ ሊበራል ዲሞክራሲ ዘመኑን የማይመጥኑ መሆናቸው
ይነገራል። ለምሳሌም ያህል፣ የመረጃ እና ተግባቦት ቴክኖሎጂ በፈጠረው አመቺነት ላይ
በመመርኮዝ ህዝቦች በመንግስታዊ ፖሊሲ ውሳኔዎች ላይ የሚኖራቸው ቀጥተኛ
ተሳታፊነት (e-Governance) እያደገ እንደሚሄድ ይጠበቃል። ከዚህም በላይ፣ አካታች
እና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም የበለጠ አሳታፊ (participatory) እና በሰፊ
መግባባት (consensus) ላይ የተመረኮዘ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አጅግ አስፈላጊ
ይሆናል። ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ከሁለቱም የዲሞክራሲ ሥርዓቶች ሊወሰዱ የሚችሉ ጠቃሚ
ተሞክሮዎች ይኖራሉ።
ሶስተኛው መዋቅራዊ ፈተና፣ አሁን በስራ ላይ ካለው ህገ መንግስት ጋር የተያያዘ
ነው። ይህን በተመለከተ፣ ባንድ በኩል አሁን ያለው ህገመንግስት በመሰረታዊ ባህሪው
ኢዴሞክራሲያዊ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እና በሌላ አዲስ ህገ መንግስት መተካት
አለበት ብለው የሚያምኑ ወገኖች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ይህ ህገ መንግስት
የብሔረሰቦችን መብት ያስከበረ በመሆኑ እርሱን ለመቀየር መሞከር ሃገሪቱን ወደ
መበታተን ሊወስዳት ይችላል የሚሉ ወገኖች አሉ። ከበርካታ የተረጋጋ መንግሥታዊ
ሥርዓት ባለቤት ከሆኑ ሃገሮች ታሪክ እንደምንማረው፣ የእነዚህ ሃገሮች ህገ መንግስት
ከጅምሩ ‘ሙሉ በኩለሄ’ ሆኖ የተፈጠረ ሳይሆን በየወቅቱ እየተሻሻለ እና እየበለፀገ የሚሄድ
ህልው (organic) ሰነድ ነው። ከዚህ አኳያ፣ በስራ ላይ ያለውን ህገመንግስት አውጥተን
እንጣለው የሚለው አቋም አሻጋሪ የመሆን እድሉ ውሱን ከመሆኑም ባሻገር እንደከዚህ
ቀደሙ አፍርሶ የመገንባት ቅኝት ያለው በመሆኑ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ሆኖ
አይታይም። ከዚህ በተጨማሪ፣ በስራ ላይ ያለው ህገመንግስት ምንም እንኳን አንዳንድ
ጉድለቶች እና ድክመቶች ያሉበት ቢሆንም፣ በርካታ ጠቃሚ እና አሻጋሪ የሆኑ የህግ
አንቀጾችን ይዟል። በመሆኑም፣ የጊዜው ትኩረት መሆን ያለበት ባለው ህገመንግስት ውስጥ
ያሉትን ድክመቶች እና ጉድለቶች ህዝብን አካታች እና አሳታፊ በሆነ ሂደት እያሻሻሉ
ጠቃሚውን እያጠናከሩ መሄድ ነው። ይህን በተመለከተ፣ በከፍል ስድስት
እንመለስበታለን።
አራተኛው ፈተና፣ በስራ ላይ ካለው ህግመንግስት ጋር በተያያዘ ሃገሪቱ ሊኖራት
የሚገባው የፌዴራል አወቃቀርን ይመለከታል። ባንድ በኩል፣ አሁን በስራ ላይ ያለው
በብሔር ላይ የተመረኮዘ የፌዴራል መዋቅር የሃገሪቱን አንድነት የሚፈታተን እና
ወደመበታተን የሚያመራ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ መቀየር አለበት ብለው የሚያምኑ ወገኖች
አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ያለው የፌዴራል አወቃቀር ለብሔሮች ራስን በራስ
የማስተዳደር መብት ያጎናጸፈ በመሆኑ እርሱን ለመቀየር መሞከር ሀገሪቱን ወደ ብጥብጥ
እና መበታተን ሊወስዳት ይችላል የሚሉ ወገኖች አሉ። መልካሙ ነገር፣ ሁለቱም ወገኖች
ለሃገሪቱ ሀገረ-መንግሥት፣ ፌደራል የመንግስት አደረጃጀት ብቸኛው አማራጭ መሆኑ ላይ
ይስማማሉ። አገራችን ባሁኑ ሰዓት ከተጋፈጠቻቸው ዋና ዋና ፖለቲካዊ ፈተናዎች አኳያ፣