Page 34 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 34
ደስታ መብራቱ
ሃገራችን አሁን በምትገኝበት ወሳኝ የፖለቲካ ምዕራፍ በእጅጉ የሚያስፈልገን
በየቦታው እየተከሰቱ ላሉት አሳዛኝ የህዝቦች ግጭት እና መፈናቀል ሁነቶች እና ሂደቶች
ዋነኛ ምንጭ የሆኑትን መዋቅራዊ ችግሮች፣ ለነኚህ መዋቅራዊ ችግሮች መነሻ የሆኑትን
የአስተሳሰብ ምንጮችን መረዳት እና ለዚህም የሚመጥን አካታች እና ፋና-ወጊ
መፍትሔዎች መሻት ነው። ይህም እንዲሳካ፣ እያንዳንዱ የፖለቲካ ተዋናይ ያሉትን
አስተሳሰቦች እና እምነቶች ከምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎች አኳያ ሊመረምራቸው እና
ሊፈትሻቸው ይገባል።
10
2.1 የህመሞቻችን ምንጮች
የሃገራችንን የፖለቲካ ችግሮች በመሰረታዊ ሁኔታ ለመፍታት የመጀመሪያው
እርምጃ የበሽታው ዋነኛ ምንጮች የሆኑ የአመለካከት እና የዕምነት መሰረታዊ እሴቶችን
(values) መመርመር ያስፈልጋል። እነኚህ እሴቶች፣ በሀገሪቱ ውስጥ ለረጅም ዘመን
ተንሰራፍተው ከቆዩት የአስተዳደር፣ የዕምነት፣ የትምህርት፣ የባህል እና የልማድ ሥርዓት
ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው። የበርካታ ብሔረሰቦች ሃገር የሆነችው ሃገራችን ኢትዮጵያ፣
የብዙ ጠቃሚ እና ድንቅ እሴቶች ባለቤት እንደሆነች ይታመናል። እንዳለመታደል ሆኖ፣
የሃገራችን ዘመናዊ ፖለቲካ፣ ጠቃሚ በሆኑ ዕሴቶቻችን ላይ ከመገንባት ይልቅ ጎጂ በሆኑ
ውርሶቻችን ተተብትቦ ይገኛል። ለዚህ እንደ ዋነኛ ምክንያት ሊጠቀሱ የሚችሉ በርካታ
አባባሽ ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ የችግሮቹ ዋነኛ አእምሮአዊ
ምንጮች የሚከተሉት ሶስት አበይት ፈተናዎች ናቸው።
ጭፍን እመርታዎች፡ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ ከዘመናዊው የትምህርት
ሥርዓት መጀመር ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው። በዘመናዊው
የትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ ያለው አንዱ መሰረታዊ ችግር የትምህርት ይዘቱንም ሆነ
አሰጣጡን ከሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ እና ሃገር በቀል እውቀት ክምችት ጋር ለማጣጣም እና
ለማዋሃድ የተደረገው ጥረት ውሱን መሆኑ ነው። ይህም በመሆኑ የሃገሪቱ የተማረ የሰው
ሃይል የሃገሪቱን የልማት ችግሮች ለመፍታት ካለው የእውቀት አቅም ውሱንነት ባሻገር
ባብዛኛው ጭፍን የሆነ የድንበር ተሻጋሪ ዘመናዊነት አምላኪ ሊሆን ችሏል። ይህ መሰረታዊ
ህመም በዘመናዊው የፖለቲካ አስተሳሰባችንም ላይ በተናጠከረ ሁኔታ ታይቷል።
በመሆኑም፣ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ከሃገራዊ እውነታ እና ተጨባጭ የህዝብ ፍላጎት ጋር
የማይጣጣሙ የፖለቲካ አስተሳሰቦች እና የማህበረሰብ እድገት ሞዴሎችን በጅምላ እና
በጭፍን ተቀብሎ ማህበራዊ መሰረቱን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ለማራመድ እና ለመተግበር
መሞከር የፖለቲካችን ዋነኛው መለያ ሊሆን ችሏል። እንዲህ ዓይነቱ አመለካከትም፣
ከ1960ዎቹ ጀምሮ በሃገራችን ለተፈጠሩት የፖለቲካ ምስቅልቅሎች ታላቁን ድርሻ
እንዳበረከተ ይታመናል።
10 የዚህ ክፍል አብዛኛው፣ ሐምሌ 11 ቀን 2012 በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ታትሟል።