Page 30 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 30
ደስታ መብራቱ
iv. እነኚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ችግሮች ተጠናክረው መውጣት ከጀመሩበት
ክ1950ዎቹ ጀምሮ በተለያዩ የሳይንስ መስኮች ሰፊ ጥናት ሲደረግባቸው
ቆይቷል። ነገር ግን፣ የችግሮቹ ውስብስብነት በአንድ የሳይንስ ዘርፍ የተቀነበበ
ትንተና (reductionism) መረዳትም ሆነ መሰረታዊ መፍትሔ ማግኘት
እንዳይቻል አድርጎታል። ይህም፣ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እየዳበረ ለመጣው
ምህዳራዊ አስተሳሰብ (systems thinking) መሰረት ሊሆን ችሏል።
v. ምንም እንኳን የሳይንስ ዋነኛው ዓላማ እውነታዎችን ወይም እውነትን መፈለግ
መሆኑ በሁሉም የሳይንስ ልሂቃን ቢነገርም እውነት ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ
በሚሰጠው መልስ ላይ ለዘመናት የዘለቀ ልዩነት ነበረ። ይህም፣ በሁለትዮሽ
እውነት (bivalent truth) እና በሁለገብ እውነት (multivalent truth)
አመክንዮ ላይ ለተመሰረቱ የሁለት ዓለሞች ፍልስፍና መሰረት ሆኖ ዘልቋል።
vi. የምዕራባዊው ሳይንስ ዋነኛ መለያ የሆነው የተቀነበበ ትንተና ተፈጥሮን የራሱ
ህልው የሂደት መርህ እንዳለው ፍጡር (organism) ሳይሆን እንደ አንድ ታላቅ
ማሺን ሊጠና እና ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል አካል አድርጎ ይወስዳል። በሌላ
በኩል ግን፣ በሁለንተናዊ አስተሳሰብ (holistic thinking) መሠረት፣
ማናቸውም ምሉዕነት ያለው ቁስ ሆነ ሕይወት የተመሰረተው የራሳቸው
ምሉዕነት ባላቸው ክፋዮች ቅንጅታዊ አደረጃጀት ነው ይላል።
vii. የምህዳራዊ አሰተሳሰብ የፍልስፍና መሰረቶች፣ ሁለትዮሽ ዕውነትን የሁለገብ
ዕውነት ጊዜያዊ መገለጫዎች፣ የተቀነበበ አስተሳሰብን የሁለንተናዊ አስተሳሰብ
ደጋፊ አካል አድርጎ በመቀበል ላይ የተመረኮዙ ናቸው። በዚህም መሰረት፣
አብዛኛው ገሃዱ ዓለም፣ የተደራጀ ውስብስነት (organized complexity)
ባላቸው ምህዳሮች የተሞላ በመሆኑ በተደራጀ ቀላልነት (organized
simplicity) ላይ የተመረኮዘ የተቀነበቡ መፍትሔዎችም ሆኑ ባልተደራጀ
ውስብስብነት (unorganized complexity) ላይ የተመረኮዙ ስታቲስቲካዊ
መፍትሔዎች በሙሉ ጊዜያዊ (tentative) እና ያልተሟሉ ይሆናሉ ብሎ
ያምናል።
viii. በምህዳራዊ አስተሳሰብ መሰረት አንድ ምህዳር ማለት የየራሳቸው ህልው
ባህርያት ያሏቸው የተለያዩ ቁሳዊ ነገሮች እና ባህርያት (attributes)
የተደራጁበት የግንኙነት ስብስብ ነው። የምህዳራዊ ትንተናም ዋነኛው መለያው
አንድን ውስብስብ ምህዳር በጥቅልነቱ ለመረዳት የሚያስችሉ መሰረታዊ
ጥያቄዎችን መጠየቁ ነው። ከነዚህም ዋነኛው፣ በጊዜ ሂደት የሚከሰቱ መሰረታዊ
መዋቅራዊ ግንኙነቶች (underlying structural relationships) እና የባህሪ
ዘይቤዎች (patterns of behavior) ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው።
ix. በተለያዩ ጥናቶች እንደተረጋገጠው፣ ህጻናት አብዛኛውን የገሃዱን ዓለም
የመጀመሪያ ዕውቀቶቻቸውን የሚያዳብሩት በቅድሚያ የምሉዕ ምህዳሩን
ስሜት ተወራራሽ በሆነ አመክንዮ (transductive logic) በመገንዘብ ነው።
ይህም፣ ሁሉም የሰው ፍጡር የሁለንተናዊ አስተሳሰብ ክህሎት በተፈጥሮ
የተሰጠው መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም፣ ለምንም ዓይነት ዘመናዊ ትምህርት